የወጣቶች እግርኳስ | 18-01-2009
የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ አላፊ ሃገራት በሳምንቱ መጨረሻ በሚደረጉ ወሳኝ የመልስ ጨዋታዎች ይለያሉ፡፡ የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድንም ከማሊ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ የሚያደርገውን ዝግጅት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ አድርሷል፡፡
በአዲስ አበባ ስታድየም እየተዘጋጀ የሚገኘው ብሄራዊ ቡድኑ በዛሬው የልምምድ መርሃ ግብር በእሁዱ ጨዋታ ላይ ቋሚ ተሰላፊዎች ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱትን በመለየት የቅንጅትና ከርቀት አክርሮ የመምታት ልምምዶችን አከናውኗል፡፡
ባለፉት ሶስት ቀናት በመጠነኛ ጉዳት በልምምድ ወቅት አቋርጠው ሲወጡ የነበሩት ሳሙኤል ተስፋዬ እና አቡበከር ነስሩ በዛሬው ልምምድ ከቡድኑ ጋር ሙሉ ልምምድ የሰሩ ሲሆን ሁሉም ተጨዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡
ከ17 አመት ቡድናችን እሁድ ዕለት ከአፍሮ ፅዮን ጋር ባደረጉት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ላይ ከአፍሮፅዮን በኩል መልካም እንቅስቃሴ ያሳዩ 6 ተጨዋቾች ጥሪ ቀርቦላቸው በዛሬው ልምምድ ላይ ተገኝተው ከቡድኑ ጋር ልምምድ ያደረጉ ቢሆንም አሳማኝ እንቅስቃሴ ባለማሳየታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
ቀይ ቀበሮዎቹ በእሁዱ ጨዋታ በባማኮ የደረሰባቸውን የ2-0 ሽንፈት ቀልብሰው ወደ ማዳጋስካር የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ለማምራት በከፍተኛ ተነሳሽነት እና ፍላጎት ዝግጅታቸውን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ለመታዘብ ችለናል፡፡
በኢትዮጵያ እና ማሊ መካከል የሚደረገው ጨዋታ እሁድ መስከረም 22 ቀን 2009 በአዲስ አበባ ስታድየም 10:00 ላይ የሚካሄድ ሲሆን ጨዋታው የሚካሄድበት የአዲስ አበባ ስታድየም ሜዳን ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የእሁዱ ተጋጣሚያችን የማሊ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አርብ አዲስ አበባ ይገባል፡፡ ጨዋታውን የሚመሩት አራቱም ዳኞች ከኒጀር ፤ ኮሚሽነሩ ደግሞ ከዩጋንዳ እንደተመደቡም ታውቋል፡፡