የአፍሪካ እግርኳስ | 19-01-2009
የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) በግብፅ ዋና መዲና ካይሮ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡ የፊፋ ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ የጋናው ክዌሲ ናያንኪ እና የጊኒው አልማሚ ካቤሌ ካማራ ለስድስት ወራት ለፊፋ ካውንስል አፍሪካን ወክለው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል፡፡ የጅቡቲ እግርኳስ ፌድሬሽን በካፍ መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 18.3 ላይ ያቀረበው የማሻሻያ ረቂቅ ደግሞ ውድቅ ሆኗል፡፡
የጋና እግርኳስ ማህበር ፕሬዝደንት እና የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ክዌሲ ናያንኪ 31 ድምፅ በማግኘት ሲያሸንፉ ጊኒያዊው የካፍ ምክትል ፕሬዝደንት አልማሚ ካማራ 37 ድምፅ በማግኘት ለፊፋ ካውንስል ተመርጠዋል፡፡ ንያንኪ የማዳጋስካሩ አህመድን በአንድ ድምፅ በመብለጥ ነው ማሸነፍ የቻሉት፡፡ ካማራ እና ናያንኪ በጥቅምት 13-15 ዙሪክ ስዊዘርላንድ ላይ በሚደረገው የፊፋ ካውንስል ስብሰባ ላይ ስራቸውን የሚጀምሩ ይሆናል፡፡
በዙሪክ በሚደረገው ስብሰባ የ2026 የዓለም ዋንጫ ወደ 40 ሃገራት የማስፋት የሚለው አጀንዳ ዋናው ነው፡፡ የፊፋ ካውንስል ሁለቱን አዲስ ተመራጮቹን ጨምሮ የካፍ ፕሬዝደንቱን ኢሳ ሃያቱ፣ ሃኒ አቦ ሪዳ (ግብፅ)፣ ኮንስታንት ኦማሪ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)፣ ታሪቅ ቦቻማኢ (ቱኒዚያ) እና ሊዲያ ንስኬራ (ቡሩንዲን) ከአፍሪካ በአባልነት ይዟል፡፡ በካውንሰሉ ውስጥም ሴኔጋላዊቷ የፊፋ ዋና ፀሃፊ ፋትማ ሳሞራ ትገኛለች፡፡
በጠቅላላው ጉባኤ በተነሳው ሌላ አጀንዳ የጅቡቲ እግርኳስ ፌድሬሽን የቀረበው የማሻሻያ ረቂቅ ውድቅ ሆኗል፡፡ ረቂቁ የካፍ ፕሬዝደንት ዕጩዎችን ከሰራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ብቻ መመረጥ አለባቸው የሚለውን ህግ ለማስቀየር የታለመ ቢሆንም በ32 ድምፅ ውድቅ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት ሃገራት በድምፀ ታቅቦ ረቂቁን አልፈውታል፡፡
ኢትዮጵያዊው ይድነቃቸው ተሰማ ከካፍ ፕሬዝደንትነት መገለል በኃላ መንበረ ስልጣኑን ያለተቀናቃኝ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ የያዙት ካሜሮናዊው ኢሳ ሃያቱ ለካፍ ፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩ እጩዎች ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ብቻ እንዲሆን ከአራት አመታት በፊት የወጣው ህግ እራሳቸውን ለመጥቀም የታለመ ነው የሚሉ ተቺዎች በስፋት ይታያሉ፡፡
ቀጣዩ የካፍ 39ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሐሙስ መጋቢት 7 2009 በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡ በአዲስ አበባ በሚኖረው ጠቅላላ ጉባኤ ላይም ለፊፋ ካውንስል አባልነት በድጋሚ ምርጫ የሚኖር ይሆናል፡፡