በሀዋሳ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የደቡብ ክልል ካስቴል ዋንጫ ነገ በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየምፍፃሜውን ሲያገኝ አርባምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ዋንጫውን ለማንሳት 09፡00 ላይ ይፋለማሉ፡፡
ትላንት በተካሄዱት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ተጋጣሚዎቻቸውን በመለያ ምቶች በመርታት ለፍፃሜ መብቃት ችለዋል፡፡
አርባምንጭ በተጋባዝነት ውድድሩ ላይ እየተካፈለ ከሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ጋር መደበኛውን የጨዋታ ክፍለጊዜ 1-1 አጠናቆ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡት የመለያ ምቶች አርባምንጭ 5-4 ማሸነፍ ችሏል፡፡ በተመሳሳይ ሲዳማ ቡና ከሌላው ተጋባዥ ቡድን ድሬዳዋ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ መደበኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1-1 አጠናቆ በመለያ ምቶች 9-8 ማሸነፍ ችሏል፡፡
በክረምቱ አርባምንጭ ከተማን ለቀው ሲዳማ ቡናን የተቀላቀሉት ትርታዬ ደመቀ እና አበበ ጥላሁን በፍፀሜው የቀድሞ ክለባቸውን በተቃራኒው የሚገጥሙ ይሆናል፡፡
ከፍጸሜው ጨዋታ በፊት 07፡00 ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ለ3ኛ ደረጃ ይፋለማሉ፡፡ በከፍተኛ ድምቀት ሲካሄድ የቆየው ውድድሩ ከፍተኛ ተመልካች ያገኘ ሲሆን ከፍተኛ ገቢ እንደተገኘበትም ታውቋል፡፡