የ2016 ኦሬንጅ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ በደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ አሸናፊነት ተጠናቅቋል፡፡ ብራዚሎቹ የግብፁ ዛማሌክን በድምር ውጤት 3-1 በማሸነፍ ነው በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮን መሆን የቻለው፡፡ ጨዋታውን ዛማሌክ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡
በግብፅ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው አሌክሳንደሪያ በተካሄደው ጨዋታ ዘ ኋይት ናይትስ በመባል የሚታወቁት ዛማሌኮች በመጀመሪያ ጨዋታ የደረሰባቸውን የ3-0 ሽንፈት ለመቀልበስ ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በባሰም ሞርሲ እና በናይጄሪያዊው ስታንሊ ኦዋዉቺ ግብ ለመሆን የቀረበ ያልተሳካ መከራ ማድረግ ችለዋል፡፡ ካማ ቢሊያት የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በዛማሌክ ተከላካዮች ተጨርፎ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ዛማሌኮች በስታንሊ ኦዋዉቺ ግብ መሪ ሲሆን በተደጋጋሚ ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከኦርላንዶ ፖይሬትስ በመቀጠል የአፍሪካ ቻምፒዮን የሆነ ሁለተኛው የደቡብ አፍሪካ ክለብ ሆኗል፡፡ ሰንዳውንስ በቻምፒየንስ ሊጉ በዲ.ሪ. ኮንጎው ኤኤስ ቪታ ክለብ ተሸንፎ ከቻምፒየን ሊጉ ምድብ ውጪ እንዲሁም ከኮንፌድሬሽን ካፕ በጋናው ሚዲአማ ተሸንፎ ከውድድሮቹ ወጥቶ ነበር፡፡ ካፍ የቪታ ክለብን ባልተገባ ተጫዋች በማሰለፉ ምክንያት ከቻምፒየንስ ሊጉ ምድብ ሲያሰናብት ሰንዳውንስ በቦታው ተተክቷል፡፡ በምድብ ሁለት ከናይጄሪያው ኢኒምባ ኢንተርናሽናል፣ ዛማሌክ እና የአልጄሪያው ሴቲፍ (በደጋፊዎች ያለተገባ ባህሪ ምክንያት ከቻምፒየንስ ሊጉ ተሰናብቷል) የተደለደለው ሰንዳውንስ ምድቡን በበላይነት ጨርሷል፡፡ በግማሽ ፍፃሜው የዛምቢያውን ዜስኮ ዩናይትድ 3-2 በማሸነፍ ወደ ዋንጫ ያደረገውን ግስጋሴ አሳምሯል፡፡
የዛማሌክ ክለብ ፕሬዝደንት የሆኑት ሞርታዳ መንሱር ጨዋታውን በመሃል ዳኝነት የመሩትን ጋምቢያዊውን ባካሪ ፓፓ ጋሳማን አብጠልጥለዋል፡፡ ባካሪ ጋሳማ የ2015 የግሎ ካፍ የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ዳኛ ነበር፡፡ በአወዛጋቢነታቸው የሚታወቁት ፕሬዝደንቱ ከመጀመሪያው ጨዋታ ሽንፈት በኃላ ክለባቸው የተሸነፈው በጂኒ እና አስማትን በተጠቀመው ሰንዳውንስ እንደሆነ መናገራቸው ቡዙዎችን አስገርሟል፡፡ ሞርታዳ ከዚህ ቀደም ወደ ግብፅ ብሄራዊ ቡድን በቅርቡ የተመለሰውን ኤሳም ኤል ሃድሪ ግቡን የሚጠብቀው በአስማት ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የ1.5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ሽልማትን ሲያገኝ በ2016 መጨረሻ በጃፖን በሚካሄደው የፊፋ የአለም ክለቦች ዋንጫ ላይ አፍሪካን የሚወክል ይሆናል፡፡ የገንዘብ ሽልማቱ ከሰንዳውንስ ባሸገር ለቀሪ ስድስት ተሳታፊ ክለቦች እንደነበራቸው ደረጃ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ በፈረንሳዩ የቴሌኮሚኒኬሽን ድርጅት ኦሬንጅ ስፖንሰር አድራጊነት ሲደረግ የነበረው ቻምፒየንስ ሊጉ በ2017 በቶታል ስፖንሰር የሚደረግ ሲሆን የነበረው ምድብም ከሁለት ወደ አራት የሚጨምር ይሆናል