በ2016 ኦሬንጅ ካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ የመጀመሪያ ዙር የፍፃሜ ጨዋታ አልጄሪያ ላይ ቅዳሜ ምሽት ተደርጎ ኤምኦ ቤጃያ እና ቲፒ ማዜምቤ 1 አቻ በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን ጨርሰዋል፡፡ በምድብ አንድ አንድ ላይ ተደልድለው የነበሩት ሁለቱ ክለቦች በቤጃያ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር ታይቶበታል፡፡
በጨዋታው ቲፒ ማዜምቤ በዲ.ሪ. ኮንጎው ኢንተርናሽናል ጆናታን ቦሊንጊ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ቀዳሚ መሆን ችሏል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ለማስቆጠር ተጭነው የተጫወቱት ባለሜዳዎቹ ቤጃያዎች በፋውዚ ያህያ ድንቅ የቅጣት ምት ግብ አቻ መሆን ችለዋል፡፡ ቤጃያ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ አስደንጋጭ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ያደረገ ቢሆንም በማዜምቤው ግብ ጠባቂ ሲልቪያል ጎቦሆ ሊከሽፉ ችለዋል፡፡ የሁለቱ ክለቦች የፍፃሜ የመልስ ጨዋታ በሚቀጥለው ሳምንት ሉቡምባሺ ላይ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ከወዲሁ የማሸነፍ ቅድመ ግምቱን ማዜምቤ ወስዷል፡፡ ቤጃያ በኮንፌድሬሽን ካፑ ያለው ከሜዳ ውጪ ሪከርድ ጥሩ የሚባል አይደለም፡፡ ቤጃያ በውድድሩ ከሜዳው ውጪ ያሸነፈው ጨዋታ የለም፡፡
በሙሉ ስሙ ሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ በመባል የሚታወቀው የአልጄሪያው ክለብ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ሲሳተፍ ይህ የመጀመሪያው ግዜ ነው፡፡ ቤጃያ ከሶስት ዓመታት በፊት ነበር ወደ አልጄሪያው ሊግ ሞቢሊስ ማደግ የቻለው፡፡ ክለቡ በሶስት ዓመታት ውስጥ የአልጄሪያ ዋንጫ እና በሊጉ የሁለተኝነት ደረጃን ማሳካት ችሏል፡፡
ቲፒ ማዜምቤ በ2013 በኮንፌድሬሽን ካፕ ፍፃሜ በቱኒዚያው ሴፋክሲየን ከተሸነፈ በኃላ በውድድሩ ሲሳተፍ ይህ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡ የአምስት ግዜ የአፍሪካ ሻምፒዮኑ ማዜምቤ በ2015 የቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል፡፡