ዩጋንዳ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከኮንጎ ብራዛቪል ጋር በሚቀጥለው ሳምንት ላለባት ጨዋታ ሰርቢያዊው የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሰርዮቪች ‹‹ሚቾ›› ሚሉቲን በቅዱስ ጊዮጊርስ እየተጫወቱ የሚገኙት ሶስት ተጫዋቾችን መጥራታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል፡፡
ግብ ጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራ፣ ተከላካዩን አይዛክ ኢዜንዴ እንዲሁም አዲስ ፈራሚው ያስር ሙገርዋን ለዩጋንዳ ክሬንስ ስብስብ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ ዩጋንዳ ህዳር 3 ከኮንጎ ብራዛቪል ጋር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዋን ከማድረጓ አስቀድሞ ከዛምቢያ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ የምታደርግ ይሆናል፡፡
የአምስት ግዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ የተመረጠው ሮበርት ሃገሩ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ባረጋገጠችበት የኮሞሮሱ ጨዋታ እንዲሁም በዓለም ዋንጫ ጨዋታ ታማሌ ላይ ከጋና ጋር አቻ በተለያየችበት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ከብሄራዊ ቡድኑ ውጪ ነበር፡፡ በዴኒስ ኦኒያንጎ ተቀድሞ ክሬንሶቹን በሁለተኛ ግብ ጠባቂነት የሚያገለግለው ሮበርት በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ፈረሰኞቹ ከጅማ አባ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ ለ45 ደቂቃዎች ተሰልፎ መጫወት ችሏል፡፡
ከኦርላንዶ ፖይሬትስ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቀለው ያስር ሙገርዋ ዳግም ለብሄራዊ ቡድን ተጠርቷል፡፡ እምብዛም ለሃገሩ ብሄራዊ ቡድን ተሰልፎ መጫወት ያልቻለው ያስር በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለጊዮርጊስ ሁለት ግዜ ተሰልፎ መጫወት ችሏል፡፡ አይዛክ ኢዜንዴ ደግሞ በሚቾ ስብስብ ውስጥ ተከላካይ ስፍራ መሪ ሲሆን በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ ከቋሚ 11 ወጥቶ አያውቅም፡፡
ዩጋንዳ ከ38 አመታት በኃላ ጋቦን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ያለፈች ሲሆን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጠንካራዋን ጋናን ከሜዳዋ ውጪ ነጥብ አስጥላለች፡፡ ሚቾ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት ከሆነ ከዛምቢያ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ለኮንጎ ብራዛቪሉ ፈተና የሚመጥኑ ተጫዋቾችን ለማየት እንደሚረዳቸው ተማምነዋል፡፡ ሶስቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ለኮንጎው ጨዋታ የሚመረጡ ከሆነ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መክፈቻ ክለባቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የሚያልፋቸው ይሆናል፡፡