‹‹ በቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ላይ አለመሳተፋችን ጫና ፈጥሮብናል›› አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዲሱ የውድድር ዘመን ሊጀመር የ15 ቀናት እድሜ ብቻ ቀርቶታል፡፡ የቅድመ ውድድር ዘመን ጨዋታዎች ላይ ያልተካፈለው ወልድያ ዝግጅት ምን እንደሚመስል እና ተያያዝ ጉዳዮችን በተመለከተ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ እኛም በርዕሶች ከፋፍለን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

‹‹ የፕሪሚየር ሊጉ መጀመርያ መራዘም ጠቅሞናል››

ሁለት ጊዜ የተራዘመው የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ ወልድያን ጨምሮ ከከፍተኛ ሊጉ ያደጉት 4ቱ ክለቦችን የጠቀመ ይመስላል፡፡ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት ከዝግጅት ጊዜ እጥረት ጋር በተያያዘ ይፈጠር የነበረውን ክፍተት በመቅረፍ በኩል አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ‹‹ የተሟላ ዝግጅት አድርገናል ባንልም ጥሩ የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት እያሳለፍን እንገኛለን፡፡ የፕሪሚር ሊጉ መጀመርያ ቀን መራዘሙም ከነበረብን የዝግጅት ጊዜ እጥረት አንጻር የፈለግነውን ስራ እንድንሰራ አግዞናል፡፡ ነገር ግን የዝግጅት ጨዋታዎች አለማካሄዳችን ትልቅ ተጽእኖ ፈጥሮብናል፡፡

በቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ላይ አለመሳተፉ ጫና ፈጥሮበታል

በፕሪሚየር ሊጉ ከሚካፈሉት 16 ክለቦች መካከል የቅድመ ውድድር ዝግጅት ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ ያልቻለው ወልድያ ብቻ ነው፡፡ በአዲሱ የውድድር ዘመን ምን አይነት መልክ ሊኖረው እንደሚችል ያልታወቀው ወልድያ በዝግጅት ጨዋታዎች አለመሳተፉ ጫና እንደሚፈጥርባቸው አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ያምናሉ፡፡ ‹‹ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ የመካፈል ፍላጎት ነበረን፡፡ ነገር ግን አስተዳደሩ በተለያዩ የክለቡ ጉዳዮች ላይ ተጠምዶ የነበረ በመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ይህም በውድድር ዘመኑ ዝግጅት ላይ ተፅእኖ ፈጥሮብናል፡፡ ሆኖም ባሉት ቀሪ ቀናት ከተለያዩ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋዎች በማድረግ ራሳችንን ለመገምገም አቅደናል፡፡ ›› ብለዋል፡፡

PicsArt_1471684536863

አዳዲስ ፈራሚዎች…

9 አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ወልድያ በርካታ የፕሪሚየር ሊግ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን በማሰባሰብ በሊጉ ለመቆየት አልሟል፡፡ አሰልጣኝ ንጉሴም አዳዲሶቹ ተጫዋቾች ከበድኑ ጋር እየተዋሃዱ መሆናቸውን ተናግረዋል ‹‹ ያስፈረምናቸው ተጫዋቾች ፕሪሚየር ሊጉን በሚገባ የሚያውቁ እና ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ከነባሮቹ ጋር ቶሎ የመግባባት በአእምሮም ሆነ በአካል ብቃት ያላቸው ውህደት ጥሩ ነው፡፡ አዲሱ የውድድር ዘመንን መጀመር እየተጠባበቅንም እንገኛለን፡፡ ››

የውድድር ዘመን እቅድ…

‹‹ የውድድር እቅዳችን በሊጉ መቆየት ነው፡፡ በ2007 ከፕሪሚየር ሊጉ ከወረድንበት ትምህርት በመውሰድ በሊጉ ለመቆየት ጠንክረን እሰራን እንገኛለን፡፡ ››

እስከ ታህሳስ አጋማሽ በአዲሱ ስታድየም አይጫወትም

የወልድያ ስፖርት ክለብ የሜዳውን ጨዋታዎች እንደሚያደርግበት የሚጠበቀው ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ስታድየም እንደታቀደለት የመጀመርያዎቹን የወልድያ የሜዳ ጨዋታዎች እንደማያስተናገድ ታውቋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀውና 22,500 ተመልካቾችን በወንበር የሚያስቀምጠው ዘመናዊው የወልድያ ስታድየም በታህሳስ አጋማሽ በይፋ የሚመረቅ በመሆኑ እስከዛው ድረስ መልካ ቆሌ የክለቡን ጨዋታዎች እንደሚያስተናግድ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *