የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ትላንት ተካሂደው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮጊስ ወደ ፍፃሜው የተሸጋገሩበትን ድል አስመዝግበዋል፡፡
09፡00 ላይ አዳማ ከተማን የገጠመው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ መደበኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1-1 አጠናቆ በመለያ ምቶች አሸንፏል፡፡ ከፍተኛ ውጥረት በነበረበት የመጀመርያ አጋማሽ ኃይል የቀላቀለ አጨዋወት እና እልህ መጋባቶች የተስተዋሉ ሲሆን በ27ኛው ደቂቃ ኄኖክ ካሳሁን ላይ የተሰራውን ከባድ ፋውል የእለቱ አርቢቴር ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ በዝምታ ማለፋቸውን ተከትሎ በተነሳ ውዝግብ የአዳማ ከተማው ተከላካይ ተስፋዬ በቀለ በሁለት ቢጫ ከሜዳ እዲወጣ ምክንያት ሆኗል፡፡ አዳማ ከተማም ለ1 ሰአት ያህል በ10 ተጫዋች ለመጫወት ተገዷል፡፡
ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የወሰዱት ኢትዮ-አሌትሪኮች ሲሆኑ ዘንድሮ ክለቡን ተላቅሎ ድንቅ አቋም እያሳየ የሚገኘው ዳዊት እስጢፋኖስ በ69ኛው ደቂቃ ከረጅም ርቀት የመታው ኳስ የግብ ጠባቂው ጃፋር ደሊል የአቋቋም እና ኳስ የመቆጣጠር ስህተት ታክሎበት ግብ ሆኗል፡፡
በ80ኛው ደቂቃ በኢትዮ-ኤሌክትሪክ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል አቅራቢያ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት አምበሉ ሱሌይማን መሐመድ መትቶ ወደ ግብነት በመቀየር አዳማን አቻ አድርጓል፡፡ ሱሌይማን ግቧን ካስቆጠረ በኋላ በስህተት ግብ ወደተቆጠረበት ግብ ጠባቂው ጃፋር አምርቶ በጋራ ደስታውን ገልጧል፡፡
የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ለ ግብ መጠናቀቁን ተከትሎ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡት የመለያ ምቶች ኢትዮ-ኤሌክትሪኮች አምስቱንም ምቶች በአግባቡ ሲጠቀሙ ሲሳይ ቶሊ የመታት የመጨረሻ የፍፁም ቅጣ ምት በጋናዊው የኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ አቡ ሱሌይማና ከሽፋለች፡፡ ኢትዮ-ኤሌክትሪክም በመለያ ምቶች 5-4 በመርታት ለፍፃሜው ማለፍ ችሏል፡፡ በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂዎች ላይ ተቀይሮ የገባው ቶጓዊው የአዳማ ከተማ ግብ ጠባቂጃኮብ ፔንዜ የተመቱበትን መለያ ምቶች ለማዳን ያሳየው ደካማ ጥረት ተመልካቹን አስገርሟል፡፡
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የዘምድሮውን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 በመሸነፍ ቢጀምርም በሒደት ራሱን አሻሽሎ ከ2001 ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ለፍፃሜው ለመድረስ በቅቷል፡፡
11፡30 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ገጥሞ 2-0 አሸንፎ ለፍጻሜው አልፏል፡፡ በደጋፊዎች ህብረዜማ ደምቆ ባመሸው ጨዋታ በርካታ የግብ ሙከራዎች እና ፈጣን እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን የአቡበከር ሳኒ ከተስፋ ሰጪ ታዳጊነት ወደ ኮከብ እየተሸጋገረ እንደሆነ ያሳየበትን ምሽት አሳልፏል፡፡
በ9ኛው ደቂቃ ከምንያህል ተሾመ የተሸገረውን ኳስ አቡበከር ሳኒ ወደ ግብነት ቀይሮ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ሲያደርግ በ35ኛው ደቂቃ በድጋሚ አቡበከር ሳኒ በተከላካዮች የተመለሰውን ኳስ በቀጥታ በመምታት የግብ ልዩነቱን ወደ 2 አሳድጎታል፡፡ አቡበከር ሳኒ በእለቱ ያስቆጠራቸውን ሁለት ግቦች ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ግቦች መጠን 5 በማድረስ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪቱን ሰንጠረዥ መምራቱን ቀጥሏል፡፡ አቡበከር በኢትዮጵያውያን ብዙም ያልተለመደውን ከመስመር ወደ ውስጥ በመግባት አደጋ መፍጠር እና ግቦች ማስቆጠርን በሲቲ ካፑ እያሳየን ይገኛል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ 7 ግቦች አስቆጥሮ 1 ግብ ብቻ ተቆጥሮበት በድንቅ አቋም ላይ የሚገኝ ሲሆን ለ5ኛ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት እየተንደረደረ ይገኛል፡፡ በመጪው እሁድም በመክፈቻው 4-1 ያሸነፈው ኢትዮ-ኤሌክትሪክን በፍጻሜው ይገጥማል፡፡
ጥቅምት 12 የጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በመጪው እሁድ ጥቅምት 27 የሚጠናቀቅ ሲሆን 08፡00 ላይ አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ3ኛ ደረጃ ፤ 10፡00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮ-ኤሌክሪክ ለዋንጫ ይጫወታሉ፡፡