የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ነገ ሲጠናቀቅ በአንድ ምድብ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ 10:00 ላይ ለዋንጫው ይፋለማሉ፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በግማሽ ፍጻሜው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በ5 ግቦች ከፍተኛ ግብ አግቢነቱን እየመራ በሚገኘው አቡበከር ሳኒ ግቦች 2-0 በመርታት ወደ ፍጻሜው ያለፈ ሲሆን በውድድሩ የመጀመርያ ቀን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ባደረገው ጨዋታ 4-1 በመርታት የስነ ልቡና የበላይነቱን ይዟል፡፡ ቡድኑ ካደረጋቸው 4 ጨዋታዎች 3 አሸንፎ 1 አቻ በመውጣት ወጥ አቋም ማሳየትም ችሏል፡፡
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከጨዋታ ጨዋታ በሒደት እየተገነባ እና አቋሙን እያሻሻለ በመምጣት ለፍጻሜው መድረስ ችሏል፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 ቢሸነፍም ከመከላከያ አቻ በመውጣት እና ጅማ አባ ቡናን በማሸነፍ ፤ በግማሽ ፍጻሜው ደግሞ አዳማ ከተማን በመለያ ምቶች በመርታት ለፍጻሜው ማለፍ ችሏል፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ የደረሰባቸውን ሽንፈት የመበቀል እድልም አግኝተዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በነገው የፍጻሜ ጨዋታ ካሸነፈ ለ5ኛ ጊዜ ዋንጫ የሚያነሳ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ ይሆናል፡፡
ከፍፃሜው ጨዋታ አስቀድሞ 08፡00 በግማሽ ፍጻሜ ሽንፈት አስተናግደው ለፍጸሜ ማለፍ ያልቻሉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማ ለ3ኛ ደረጃ ይጫወታሉ፡፡