የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ትላንት ሲጠናቀቅ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቅዱስ ጊዮርጊስን 2-0 በመርታት ለ3ኛ ጊዜ የከተማው ቻምፒዮን ሆኗል፡፡
ከፍጻሜው በፊት 08:00 ላይ በተደረገው የደረጃ ጨዋታ በአመዛኙ ወጣት ተጫዋቾችን የተጠቀመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ውድድሩን በ3ኝነት አጠናቋል፡፡ የሃምራዊዎቹን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው ሲሳይ ዋጆ በ66ኛው ደቂቃ ነው፡፡
10:00 ላይ በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቅዱስ ጊዮርጊስ! 2-0 አሸንፏል፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ብልጫ የነበረውና ውብ እንቅስቃሴ ያሳየው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ35ኛው ደቂቃ በአይቮሪኮስታዊው ኢብራሂም ፎፋኖ ግብ ቀዳሚ መሆን ችሏል፡፡ ለግቡ መቆጠር የግብ ጠባቂው ዘሪሁን የትኩረት ማነስ የሚጠቀስ ነበር፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫና መፍጠር ቢችልም የኤሌክትሪክን ጠንካራ መከላከል በመስበር ይህ ነው የሚባል ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአንፃሩ በጠንካራ መከላከል እና መልሶ ማጥቃት ውጤታቸውን ለማስጠበቅ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ በ87ኛው ደቂቃ ኢብራሂም ፎፋኖ የዘሪሁን ታደለን ስህተት ተጠቅሞ የኤሌክትሪክን አሸናፊነት አብስሯል፡፡ ጨዋታውም በኤሌክትሪክ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በመክፈቻው እለት በቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰባቸው የ4-1 ሽንፈት በኋላ ከፍተኛ መሻሻል ያሳዩት ኤሌክትሪኮች ሽንፈታቸውን በመበቀል ለ3ኛ ጊዜ ቻምፒዮን ለመሆን በቅተዋል፡፡ ከ2001 በኋላም ከዋንጫ ጋር መገናኘት ችለዋል፡፡
ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ በተካሄደው የሽልማት ስነ ስርአት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ዘንድሮ የተቀላቀለውና በፍጥነት ተጽእኖ ፈጣሪነቱን ያሳየው ኢብራሂም ፎፋኖ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ሲመረጥ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቡበከር ሳኒ በ5 ግቦች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ፣ አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ የውድድሩ ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተረክበዋል፡፡ የእለቱ አምበል በረከት ተሰማም ዋንጫውን ከፍ በማድረግ የእለቱ መርሃ ግብር ፍጻሜ ሆኗል፡፡