ቲፒ ማዜምቤ የኮንፌድሬሽን ካፕ ቻምፒዮን ሆነ

የዲ.ሪ. ኮንጎው ሃያል ክለብ ቲፒ ማዜምቤ የ2016 ኦሬንጅ ካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ማዜምቤ የአልጄሪያውን ሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያን በሜዳው እና ደጋፊው ፊት 4-1 በሆነ ውጤት እንዲሁም በአጠቃላይ ውጤት 5-2 በማሸነፍ ነው የኮንፌድሽን ካፑን ማንሳት የቻለው፡፡

በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ 1 አቻ የተለያዩት ሁለቱ ክለቦች የመልሱ ጨዋታ የማሸነፍ ሰፊ ቅድመ ግምት የወሰደው ቲፒ ማዜምቤ ነበር፡፡ ሉቡምባሺ በሚገኘው ስታደ ቲፒ ማዜምቤ በተደረገው ጨዋታ ማዜምቤዎች ከተጋጣሚያቸው ቤጃያ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ ቲፒ ማዜምቤ የመጀመሪያው አጋማሽን በጁንየር ቦፔ እና ሬንፎርድ ካላባ ግቦች 2-0 መሪነት ጨርሰዋል፡፡ በተለይ ዛምቢያዊው ካላባ ያስቆጠራት ግብ ማራኪ ነበረች፡፡ ካላባ በሁለተኛው አጋማሽ መሪነቱን ወደ ሶስት ሲያሰፋ ቤጃያ በሶፊያን ከድር ግብ ውጤቱን ማጥበብ ችለው ነበር፡፡ የዲ.ሪ. ኮንጎ ኢንተርናሽናል ጆናታን ቦሊንጊ አራተኛው እና የማሰረጊያው የማዜምቤ ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡

linkdev-imagesgallery_1033_134aac9a-ef80-4f2d-a6e9-79e1a532b16e

ቲፒ ማዜምቤ 2016ን የጀመረው በካፍ ሱፐር ካፕ የቱኒዚያውን ኤቷል ደ ሳህልን በማሸነፍ ነበር፡፡ ማዜምቤ ከካፍ ቻምፒየንስ ሊግ በሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ ከውድድር በመውጣቱ ወደ ኮንፌድሬሽን ካፕ ሊወርድ ችሏል፡፡ በኮንፌድሬሽን ካፑ ሃያልነቱን ያሳየው ማዜምቤ ተጋጣሚዎቹን ለማሸነፍ ሲቸገር አልተስተዋለም፡፡ ቲፒ ማዜምቤ የክለቡ ባለቤት ሞይስ ካቱምቢ ከኮንጎ ከፕሬዝደንት ጆሴፍ ካቢላ ጋር በገቡት ቅራኔ ምክንያት ከሃገራቸው የተሰደዱበት ቢሆንም አመቱን ዋንጫ በማንሳት ጨርሷል፡፡ ውድድሩን በተለይ ካለፉት አስር አመታት ወዲህ በተደጋጋሚ ማንሳት የቻሉት የሞሮኮ፣ ግብፅ እና ቱኒዚያ ክለቦች ነበሩ፡፡ የሰሜን አፍሪካ ክለቦችን የበላይነት ተቋቁመው ዋንጫ ማንሳት የቻሉት የማሊው ስታደ ማሊያን፣ የኮንጎ ብራዛቪሉ ኤሲ ሊዮፓርድስ እና ቲፒ ማዜምቤ ብቻ ናቸው፡፡

በ2017 ኮንፌድሬሽን ካፑ በቶታል ስያሜነት የሚካሄድ ሲሆን ቲፒ ማዜምቤ ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንቶ የቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ማሜሎዲ ሰንዳውንስን በመጋቢት ወር በካፍ ሱፐር ካፕ የሚገጥም ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *