ሩሲያ ለምታስተናግደው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን የሚደረጉት የምድብ ጨዋታዎች አርብ ምሽት አልጄሪያ ላይ በተደረገ አንድ ጨዋታ ተጀምረዋል፡፡ በአምስት ምድቦች ተከፍሎ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የማጣሪያ ጨዋታዎች በመስከረም ወር የተጀመሩ ናቸው፡፡
ምድብ አንድ
ምድቡ ሁለት የሰሜን አፍሪካ ሃገራትን ይዟል፡፡ ዲ.ሪ ኮንጎ፣ ቱኒዚያ፣ ሊቢያ እና ጊኒ በምድቡ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ቱኒዚያ እና ዲ.ሪ. ኮንጎ ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫ መሳተፍ የቻሉ ሁለት ሃገራት ናቸው፡፡ ዓርብ በተደረገ ጨዋታ ቱኒዚያ ሊቢያን አልጄሪያ ላይ በተደረገ ጨዋታ 1-0 ማሸነፍ ችላለች፡፡ በሊቢያ ባለው ያለመረጋጋት የሃገሪቱ ክለቦች እና ብሄራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ ለማድረግ መገደዱ ይታወሳል፡፡
በስታደ ኦማር ሃምዲ በተደረገው ጨዋታ ሊቢያ በመጀመሪያው አጋማሽ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረግ የተሻለች ነበረች፡፡ ከዕረፍት መልስ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት የካርቴጅ ንስሮቹ በዋህቢ ካዚሪ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል፡፡ በአሰልጣኝ ሉካስ ፔጃክ የሚሰለጥኑት ቱኒዚያዎች ምድቡን መምራት ችለዋል፡፡
በምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ዲ.ሪ. ኮንጎ ወደ ኮናክሬ አምርታ ጊኒን ዕሁድ ዕለት ትገጥማለች፡፡ ጊኒ በምድብ መክፈቻ ጨዋታ በቱኒዚያ ሽንፈት ደርሷባታል፡፡ ከጨዋታ ጨዋታ በጥንካሬዋ እየታወቀች የምትገኘው ኮንጎ ሊቢያን 4-0 ማሸነፏ ይታወሳል፡፡
ምድብ ሁለት
ምድብ ውስጥ ከሚገኙት አራት ሃገራት መካከል ሶስቱ በዓለም ዋንጫው ከአንድ ግዜ በላይ ተሳትፈው ያውቃሉ፡፡ በምድቡ ውስጥ ናይጄሪያ፣ ካሜሮን፣ አልጄሪያ እና ዛምቢያ መገኘታቸው ሲታከልበት አጎጊነቱ ጨምሯል፡፡ በመጀመሪያው የምድብ መክፈቻ ጨዋታ ናይጄሪያ ከሜዳዋ ውጪ ንዶላ ላይ ዛምቢያን 2-1 ስትረታ ካሜሮን እና አልጄሪያ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
ዛሬ ናይጄሪያ አልጄሪያን ስታስተናግድ ካሜሮን ዛምቢያን ትገጥማለች፡፡ ናይጄሪያ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ባትችልም ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋቾችን ማግኘት መቻሏ አልጄሪያን ለመፈተን በቂዋ ይመስላል፡፡ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙት ኬሌቺ ኢያናቾ እና ቪክቶር ሞሰስን የያዙት ሱፐር ኢግልሶቹ ከአልጄሪያ ላይ ሶስት ነጥብ ለመውሰድ የተሻለ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ አልጄሪያ ከካሜሮን ጋር ብሊዳ ላይ 1 ኣቻ ከተለያየች በኃላ አሰልጣኝ ሚሎቫን ራይቫክን ያሰናበታች ሲሆን በአዲሱ አሰልጣኝ ጆርጅስ ሊከንስ እየተመራች ወደ ሜዳ ትገባለች፡፡ ለሰሜን አፍሪካ እግርኳስ እንግዳ ያልሆኑት አሰልጣኝ ሊከንስ ብድናቸው ከወዲሁ ነጥብ መሰብሰብ ካልቻለ ወደ ዓለም ዋንጫ የማምራቱ ጉዳይ አጣብቂኝ ይሆናል፡፡
ካሜሮን ከሞላ ጎደል የምድብ ማጣሪያዋን በስኬት ጀምራለች፡፡ ካሜሮን በሜዳዋ ዛምቢያን የማሸነፍ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷታል፡፡ የዛምቢያ ሬንፎርድ ካላባ ሃገሩ ከሜዳዋ ውጪ የትኛውንም ቡድን የመፈተን አቅም እንዳላት ቢናገርም በቅርብ ግዜያት በተደረጉ ጨዋታዎች ቺፖሎፖሎዎቹ ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡
ምድቡን ናይጄሪያ በሶስት ነጥብ ስትመራ ካሜሮን እና አልጄሪያ በአንድ ነጥብ ተከታዮቹን ደረጀዎች ይዘዋል፡፡
ምድብ ሶስት
በምድቡ መጀመሪያ ጨዋታ ኮትዲቯር ማሊን 2-1 ስትረታ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ጋቦን ከሞሮኮ ጋር አቻ ተለያይታለች፡፡ ዝሆኖቹ ወደ ማራካሽ በማምራት የአትላስ አንበሶቹን የሚገጥሙ ሲሆን ማሊ ባማኮ ላይ ጋቦንን ታስተናግዳለች፡፡ የሞሮኮው አሰልጣኝ ሆርቬ ሬናርድ ከሁለት ዓመት በፊት ለአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮንነት ያበቋት ኮትዲቯርን የሚያገኙ ይህናል፡፡ ሞሮኮ በሜዳዋ የማሸነፍ ሪከርዷ የተሻለ መሆኑን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ማሳየት ችላለች፡፡ ኮትዲቯር ጀርቪኒሆን በጉዳት ምክንያት በጨዋታው ላይ ታጣለች፡፡ ሁለቱም የምድቡ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ፡፡
ምድብ አራት
በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ከሜዳዋ ውጪ ቡርኪናፏሶን ነጥብ ስታስጥል ሴኔጋል ኬፕ ቬርድን 2-0 ማሸነፍ ችላለች፡፡ ዛሬ በሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች ኬፕ ቬርድ ቡርኪናፋሶን ስታስተናግድ ደቡብ አፍሪካ ሴኔጋልን የምትገጥምበት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡ ሴኔጋል በሰይዶ ማኔ እየተመራች ደቡብ አፍሪካን የምትገጥምበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
ምድብ አምስት
ብቸኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ዩጋንዳ የምትገኝበት ምድብ ነው፡፡ ምድቡ ጋና፣ ግብፅ እና ኮንጎ ብራዛቪልን በተጨማሪ ይዟል፡፡ በመክፈቻ ጨዋታ ጋናን ከሜዳዋ ውጪ ነጥብ ያስጣለችው ዩጋንዳ ኮንጎ ብራዛቪልን ታስተናግዳለች፡፡ ግብፅ ኮንጎ ብራዛቪልን 2-1 በማሸነፍ የምድቡ አናት ላይ የምትገኝ ሲሆን ጋናን አሌክሳንደሪያ ላይ የምትገጥምበት ጨዋታ ከአሁኑ ተጠባቂ ሁኗል፡፡
ዩጋንዳ ማክሰኞ ዕለት በአቋም መለኪያ ጨዋታ በዛምቢያ 1-0 ተሸንፋለች፡፡ በጨዋታው ሰርቢያዊው የክሬንሶቹ አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቺ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹን ሮበርት ኦዶንካራ እና አይዛክ ኢዜንዴ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አስገብተው ነበር፡፡ ሚቾ ቡድናቸው በጋና ላይ ያሳዩትን ድንቅ ብቃት መድገም ፍላጎታቸው ነው፡፡ ሚቾ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅታቸውን በጥሩ መልኩ መጓዙን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ኮንጎ ብራዛቪል ለዩጋንዳው ፈተና በፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸው ፎሮቦሬ ዶሬ እና ቱዮቪ ቢፎማ ላይ ከፍተኛ ዕምነት ጥለዋል፡፡
ግብፅ እና ጋና ዕሁድ የሚገናኙ ይሆናል፡፡ በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሶስት ዓመት በፊት ጋና ግብፅን 7-3 በሆነ የአጠቃላይ ውጤት በማሸነፍ ወደ አለም ዋንጫ ያለፈች ሲሆን ግብፅ ይህንን ታሪክ ለመሻር ወደ ሜዳ ትገባለች፡፡ ፈርኦኖቹ በአርጀንቲናዊው አሰልጣኝ ሆክቶር ኩፐር እየተመሩ ከፍተኛ መሻሻልን ያሳዩ ሲሆን ወደ ነገሱበት የአፍሪካ ዋንጫ መመለስም ችለዋል፡፡ ግብፅ የአውሮፓ እግርኳስ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች መሰብሰቧ ጋናን የማሸነፍ አቅም እንዲኗሯት አስችሏል፡፡ በጣሊያን ሴሪ አ ቦሎኛ ላይ ባሳለፍነው ሳምንት ሃትሪክ መስራት የቻለው መሃመድ ሳላ በግብፅ በኩል ይጠበቃል፡፡ ጋና ኬቬን ፕሪንስ ቦአቴንግን ዳግም ወደ ብሄራዊ ቡድን ጠርታለች፡፡ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ያሉት አሰልጣኝ አቭራም ግራንት ግብፅን ማሸነፍ ከጫናው እንዲላቀቁ ባያደርጋቸውም ከጫናው ለመላቀቅ የሚያደርጉትን ጉዞ ያሳምርላቸዋል፡፡
የአርብ ውጤት
ሊቢያ 0-1 ቱኒዚያ (ስታደ ኦማር ሃምዲ, አልጀርስ)
(50 ዋህቢ ካዚሪ ፍ.ቅ.ም.)
ቅዳሜ ህዳር 3/2009
14፡00 – ኬፕ ቬርድ ከ ቡርኪናፋሶ (ስታዲዮ ፕሪያ, ፕሪያ)
15፡00 – ደቡብ አፍሪካ ከ ሴኔጋል (ፖልክዋኔ ስታዲየም, ፓልክዋኔ)
16፡00 – ዩጋንዳ ከ ኮንጎ ሪፐብሊክ (ማንዴላ ናሽናል ስታዲየም, ካምፓላ)
16፡00 – ካሜሮን ከ ዛምቢያ (ሊምቢ ኦምኒስፖርትስ ስታዲየም, ሊምቢ)
17፡30 – ናይጄሪያ ከ አልጄሪያ (አክዋ ኢቦም ስታዲየም, ኦዮ)
18፡30 – ማሊ ከ ጋቦን (ስታደ 26 ማርች, ባማኮ)
20፡00 – ሞሮኮ ከ ኮትዲቯር (ግራንድ ስታደ ማራካሽ, ማራካሽ)
ዕሁድ ህዳር 4/2009
17፡30 – ጊኒ ከ ዲ.ሪ. ኮንጎ (ስታደ 28 ሴፕቴምበር, ኮናክሬ)
18፡00 – ግብፅ ከ ጋና (ቦርጅ ኤል አረብ ስታዲየም, አሌክሳንደሪያ)