ሩሲያ በ2018 ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉት የአፍሪካ ዞን የምድብ ጨዋታዎች ቅዳሜ እነ ዕሁድ ቀጥለው ተደርገዋል፡፡ ዩጋንዳ፣ ናይጄሪያ፣ ግብፅ፣ ዲ.ሪ. ኮንጎ፣ ብርኪናፋሶ፣ ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ ወሳኝ የሆኑ ሶስት ነጥቦችን ያገኙበትን ድል በሜዳቸው አስመዝግበዋል፡፡
ምድብ 1
ዓርብ በተረገ አንድ ጨዋታ ቱኒዚያ በዋሂብ ካዝሪ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ሊቢያን 1-0 አሸንፋለች፡፡ በምድቡ ሌላ ጨዋታ ዛሬ ኮናክሬ ላይ ዲ.ሪ. ኮንጎን ከመመራት ተነስታ ጊኒን 2-1 ረታለች፡፡ ጊኒ ሴዶባ ሶማ የ23ኛ ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ብትመራም ኮንጎዎች በንስኬንስ ከባኖ እና ያኒክ ቦላሴ በሁለተኛው አጋመሽ አከታትለው ያስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው እንዲወጡ አስችሏቸዋል፡፡ ምድቡ ከወዲሁ የሁለት ፈረሰኞች ትግል ይመስላል፡፡ ዲ.ሪ. ኮንጎ እና ቱኒዚያ ምድቡን በግብ ክፍያ ተበላልጠው በስድስት ነጥብ ይመራሉ፡፡
ምድብ 2
የምድቡ ሁለት ተጠባቂ ጨዋታዎች ቅዳሜ ተደርገዋል፡፡ ናይጄሪያ በሜዳ እና ደጋፊዋ ፊት አልጄሪያን 3-1 በማሸነፍ የምድብ መሪነቷን አጠናክራለች፡፡ ቪክቶር ሞሰስ እና ጆን ኦቢ ሚካኤል ሱፐር ኢግሎሶቹ 2-0 መሪ መሆን የቻሉበትን ግቦች በመጀመሪያው አጋማሽ ማሽቆጠር ችለዋል፡፡ በጀርመን ቦንደስ ሊጋ ለሻልክ 04 ድንቅ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ነቢል ቤንታሌብ ልዩነቱን በ66ኛው ደቂቃ ቢያጠብም የሞሰስ ሶስት ግብ ናይጄሪያን የሙሉ ሶስት ነጥብ ባለቤት አድርጓታል፡፡
በምድቡ ሌላ ጨዋታ ካሜሮን ሊምቢ ላይ ከዛምቢያ ጋር 1-1 ወጥታለች፡፡ ቺፖሎፖሎዎቹ በኮሊንስ ሙቤዙማ ግብ ቀዳሚ ቢሆኑም የማይበገሩት አንበሶቹ በቬንሶን አቡበከር የፍፁም ቅጣት ምት አንድ ነጥብ ይዘው ወጥተዋል፡፡
ምድቡን ናይጄሪያ በስድሰት ነጥብ ስትመራ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት ካሜሮን፣ ዛምቢያ እና አልጄሪያ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡
ምድብ 3
የተጠበቀው የሞሮኮ ከ ኮትዲቯር እንዲሁም የማሊ ከ ጋቦን ጨዋታ ያለምንም ግብ ተጠናቅቋል፡፡ ይህ ምድብ በሁለተኛው መርሃ ግብር ግብ ያልተቆጠረበት ምድብ ሆኗ አልፏል፡፡ የፊፋው ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በእንግድነት በተመለከቱት የማካራሹ ጨዋታ ግሽሚያ እና ጥቂት የግብ ማግባት ሙከራዎች ብቻ በሞሮኮ እ ኮትዲቯር በኩል ታይቷል፡፡ ባማኮ ላይ በተደረገው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ማሊ ያገኙትን እድሎች በግብ አናት ሲሰዱ አምሽተዋል፡፡
ምድቡን ኮትዲቯር በአራት ነጥብ ስትመራ ጋቦን እና ሞሮኮ በሁለት ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡
ምድብ 4
ያልተጠበቀ ውጤት የተመዘገበበት ምድብ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ባልተጠበቀ መልኩ ሴኔጋልን 2-1 ስታሸነፍ ወደ ኬፕ ቬርድ ደሴቶች ያመራቸው ቡርኪናፋሶ 2-0 ድል አድርጋ ተመልሳለች፡፡ ደቡብ አፍሪካ ፖልኩዋኔ ላይ ሴኔጋልን ማሸነፍ በቻሉበት ጨዋታ የድል ግቦቹን ቱላኒ ሃልትሻዋዮ እና ቱላኒ ሴሬሮ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ በሁለት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ በማጣሪያ ጨዋታዎች ሽንፈትን ለቀመሰችው ሴኔጋል ሼክ ንዶዬ በሁለተኛው አጋማሽ አስቆጥሯል፡፡
ቡርኪናፋሶ በባኑ ዲያዋራ እና ፕሪጁስ ናኩልማ የመጀመሪያ አጋማሽ ግቦች ኬፕ ቬርድን 2-0 አሸንፈዋል፡፡ ምድቡን ቡርኪናፋሶ እና ደቡብ አፍሪካ በአራት ነጥቦች በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሲመሩ ሴኔጋል በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ነች፡፡
ምድብ 5
ዩጋንዳ እና ግብፅ ወሳኝ የሆነ ድልን ኮንጎ ሪፐብሊክ እና ጋና ላይ አስመዝግበዋል፡፡ ዩጋንዳ ኮንጎ ብራዛቪልን 1-0 ካምፓላ ላይ ረታለች፡፡ በዴኒስ ኦኒያንጎ ጉዳት ምክንያት የክሬንሶቹን ግብ የጠበቀው ሮበርት ኦዶንካራ ነበር፡፡ አይዛክ ኤዜንዴም በቋሚ 11 ውስጥ መግባት ችሏል፡፡ የክሬንሶቹን የድል ግብ ፋሩክ ሚያ በ17ኛው ደቂቃ በድንቅ ሁኔታ አስቆጥሯል፡፡ ሚያ ከጆዮፍሪ ማሳ ጋር ተቀናጅተው ያስቆጠራት ግብ ከቡዙዎች አድናቆት ተችሮታል፡፡ ኦዶንካራ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴን አሳይቷል፡፡
አሌክሳንደሪያ ላይ ግብፅ ጋናን እንደተጠበቀው 2-0 አሸንፋለች፡፡ ከፍተኛ የራስ መተማመን የነበራቸው ፈርኦኖቹ በልማደኛው መሃመድ ሳላ የፍፁም ቅጣት ምት እና በአብደላ ኤል ሳይድ የጨዋታ ግቦች 2-0 ጥቋቁር ከዋክብቶቹን ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ድሉ በአርጀንቲናዊው ሄክቶር ኩፐር ለምተሰለጥነው የሰባት ግዜ የአፍሪካ ሻምፒዮኗ ግብፅ የምድቡ መሪነት ከዩጋንዳ ስትቀበል ጋና እና እስራኤላዊው አሰልጣኝ አቭራም ግራንት አጣብቂኝ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ የግራንት የጋና ቆይታ ላይም ጥያቄ አስነስቷል፡፡
ምድቡ በጋና እና በግብፅ መካከል ለአለም ዋንጫ ላማለፍ የሚደረገው ትግል ቢባልም በጠንካራ አቋም ላይ ያለቸው ዩጋንዳ የምድቡን ሚዛን የለወጠች ይመስላል፡፡ በተመዘገበው ውጤትም አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቾ ደስተኛ ሁነዋል፡፡ ግብፅ ከ1990 የጣሊያኑ የዓለም ዋንጫ አልጄሪያን አሸንፋ ካለፈች በኃላ ወደ ዓለም ዋንጫው አልፋ አታውቅም፡፡ ፈርኦኖቹ በ2010 በገልለተኛ ሜዳ ሱዳን ላይ በተደረገ የማጣሪያ ጨዋታ በአልጄሪያ እንዲሁም በ2014 በጋና ተሸንፈው ከዓለም ዋንጫው ቀርተዋል፡፡
ውጤቶች
ሊቢያ 0-1 ቱኒዚያ
ኬፕ ቨርድ 0-2 ቡርኪናፋሶ
ደቡብ አፍሪካ 2-1 ሴኔጋል
ዩጋንዳ 1-0 ኮንጎ ሪፐብሊክ
ካሜሮን 1-1 ዛምቢያ
ናይጄሪያ 3-1 አልጄሪያ
ማሊ 0-0 ጋቦን
ሞሮኮ 0-0 ኮትዲቯር
ጊኒ 1-2 ዲ. ሪ. ኮንጎ
ግብፅ 2-0 ጋና