በመሃመድ አህመድ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዳሜ እና እሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጀመር ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው ወልድያ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መልካ ቆሌ ላይ አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል፡፡
የወልድያን አርማና ባንዲራ በያዙ በርካታ የወልድያ ደጋፊዎች ደምቆ በተጀመረው ጨዋታ የጨዋታው ኮከብ የነበረው እና በዚህ የውድድር አመት ከባህርዳር ወልድያ የተቀላቀለው የተከላካይ አማካዩ ገና በ2ኛው ደቂቃ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በሁለቱም በኩል ረጃጁም ኳሶችን መሰረት ያደረገ ጨዋታ የተስተዋለ ሲሆን ወልድያዎች ወደ ግብ በመድረስ እና ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በማድረግ የተሻሉ ነበሩ፡፡ ከዳንኤል በግሩም ሁኔታ የተሻገረውን ኳስ አንዱአለም ንጉሴ ወደ ጎል ሞክሮ ግብ ጠባቂው ሙሴ ገብረኪዳን ያወጣበት በ18ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል የሄደውን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ኳስ አምበሉ ዮሃንስ ኃይሉ ወደ መሀል አሻምቶ ጫላ ወደ ጎል ሲሞክር ሙሴ ገብረኪዳን በግሩም ብቃት ባንክን የታደገበት ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ፡፡ ባንኮች የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በ23ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር በኩል የሞከሩ ሲሆን በእለቱ ጥሩ ሁኖ የዋለው በወልድያው ግብ ጠባቂ ቢሌንጌ ግብ ከመሆን አድኖታል፡፡
በጉዳት ከሜዳ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ጥሩ የነበው ጫላ ከምንያህል የተሻገረለትን ኳስ ሞክሮ በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ለእረፍት ሊወጡ 3 ደቂቃ ሲቀር ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ቢሌንጌ በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሉ ባንኮች የግብ አጋጣሚ ቢያገኙም የተከላካይ ክፍሉን በአግባቡ ሲመራው የነበረው አዳሙ ሙሀመድ አውጥቶታል፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ የተቀዛቀዘ እና በዙም ሙከራወች ያልታዩበት ሲሆን በ61ኛው በረዥሙ ወደ ግብ የተላከውን ኳስ በድሩ ኑርሀሰን ከተከላካዩች ጋር ተጋጭቶ ሲመለስ አንዱአለም ንጉሴ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ኳሷን በግብ ጠባቂው አናት ላይ በመስደድ ብቸኛዋን የወልድያ የማሸነፍያ ግብ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡
በ67ኛው ደቂቃ ንግድ ባንኮች አቻ ለመሆን የሚያስችላቸውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም ሳይችሉ ሲቀሩ ከ1 ደቂቃ በኃላ ወልድያ በግራ መስመር በኩል ወጣቱ ያሬድ ሀሰን ያሻማው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሷል፡፡ ከዚህ በኃላ የአቻነት ግብ ለማግኘት የጣሩት ባንኮች በፒተር ኑዋዲኬ አማካኝነት በ75ኛው ደቂቃ ያገኙትን የቅጣት ምት ቢሊንጌ ካዳነው ውጪ በጨዋታው ጠንካራ የነበረውን የወልድያ ተከላካይ አልፈው የግብ እድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ታይተዋል፡፡
ድሉን ተከትሎ ወልድያ ከ2007 በተለየ መልኩ የውድድር ዘመኑን በድል መክፈት ችሏል፡፡ ከ2 አመት በፊት ወልድያ በፕሪሚየር ሊጉ መክፈቻ በደደቢት 6-1 የተሸነፈ ሲሆን የመጀመርያ ድሉን ለማግኘት ረጅም ሳምንታት ለመጠበቅ ተገዶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡