የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ2009 የውድድር ዘመን ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡
20 ክለቦች የሚሳተፉበት የዘንድሮ የውድድር ዘመን በ2 ምድቦች የተከፈለ ሲሆን ካለፉት አመታት በተለየ በርካታ ክለቦች እና አዳዲስ የውድድር አሰራሮች ተግባራዊ ይደረጉበታል፡፡ የማጠቃለያ ውድድር የማይኖር ሲሆን የየምድቦቹ አሸናፊዎች ለዋንጫው እርስ በእርስ የሚጫወቱ ይሆናል፡፡
የመክፈቻ ስነስርአቱ ነገ 09፡00 በአዲስ አበባ ስታድየም ሲካሄድ በምድብ ሀ የአምናው ቻምፒዮን ደደቢት ክብሩን የማስጠበቅ ጉዞውን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ይጀምራል፡፡ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ደግሞ 10፡00 ላይ አምና 3ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው መከላከያ የሊጉ አዲስ ክለብ ቦሌ ክፍለከተማን ይገጥማል፡፡ ባህርዳር ላይ የፈረሰው ዳሽን ቢራ ሴቶች ቡድንን የተረከበው ጥረት ኮርፖሬት 09፡00 ላይ ሌላኛው አዲስ የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን በአፄ ቴዎድሮስ ስታድየም ሲያስተናግድ አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ አዳማ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማን በተመሳሳይ 09፡00 ያስተናግዳል፡፡ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ48 ሰአት ውስጥ በሁለቱም ፆታ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ ቅዳሜ የሴቶቹ ሲካሄድ እሁድ የወንዶቹ ይከናወናል፡፡
በምድብ ለ በዚህ ሳምንት መደረግ ከነበረባቸው 5 ጨዋታዎች ሶስቱ እሁድ ሲደረጉ ሁለቱ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግረዋል፡፡ አበበ ቢቂላ ላይ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ከ ልደታ ክፍለ ከተማ በ08፡00 ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ10፡00 ሲጫወቱ አዲሶቹ የሊጉ ተሳታፊዎች ጌዲኦ ዲላ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ ዲላ ላይ በ09፡00 ይፋለማሉ፡፡ በውስጥ ውዝግብ የታመሰው አዲስ አበባ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር አርባምንጭ ላይ ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ሲሸጋገር ሲዳማ ቡና በዝግጅት ጊዜ እጥረት ምክንያት የመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ እንዲተላለፍለት በጠየቀው መሰረት በሲዳማ ደርቢ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታም ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡