በካሜሩን አስተናጋጅነት የሚሄደው 10ኛው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ነገ ሲጀመር የመክፈቻውን ጨዋታ ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል አርቢቴር ሊዲያ ታፈሰ እንድትመራ በካፍ ተመርጣለች፡፡
ካፍ በድረ-ገፁ እንዳስነበበው ከ1997 ጀምሮ የኢንተርናሽናል ዳኛ የሆነችው ሊድያ ታፈሰ በያውንዴ ከተማ በሚገኘው አማሁዶ አሂጆ ኦምኒስፖርት ስታድየም የሚደረገውን የካሜሩን እና ግብፅ ጨዋታ ከማላዊ እና ማዳጋስካር ረዳት ዳኞች ጋር ትመራለች፡፡
የ2008 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ዳኛ ሊዲያ ስኬታማ የዳኝነት ጊዜያት በማሳለፍ ላይ ትገኛለች፡፡ በ2015 በካናዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአለም ሴቶች ዋንጫ ጨዋታ ላይ ጨዋታዎች መምራት የቻለች ሲሆን በኦክቶበር ወር በጆርዳን አስተናጋጅነት በተካሄደው የአለም ከ17 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ላይ እንዲዳኙ ከተመረጡ 2 አፍሪካዊያን አንዷ መሆን ችላ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ትልቅ ግምት የሚሰጠውን የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ መክፈቻ እንድትመራ ተመርጣለች፡፡