የዓምናው ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ መከላከያን በአዲስ አበባ ስታዲየም በመርታት የሊግ ጅማሮውን አሳምሯል፡፡ ፈረሰኞቹ ጦሩን 3-0 በማሸነፍ ከወዲሁ የፕሪምየር ሊግ መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ሁለቱ ክለቦች ኢትዮጵያን በአፍሪካ የክለቦች ውድድር መድረክ የሚወክሉ ሲሆን ፍጥጫቸው ሁሌም ጠንካራ ፉክክር የሚታይበት ነው፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ጥቂት የግብ እድሎችን ብቻ ያስመለከተ ሆኖ አልፏል፡፡ ፈረሰኞቹ በ8ተኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር፡፡ አዳነ ግርማ በጥሩ የመልሶ ማጥቃት የመጣውን እድል ተጠቅሞ የሞከረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ታካ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡ ከደቂቃ በኃላ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በመሃል ተከላካይነት ፈረሰኞቹን እያገለገለ የሚገኘው ምንተስኖት አዳነ የሞከረው ሙከራ የመከላከያው ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ መልሶበታል፡፡ በ37ኛው ደቂቃ የቅዱስ ጊዮርጊሱ መሃሪ መና ምንይሉ ወንድሙ ላይ ያልተገባ ጥፋት በመፈፀሙ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡
ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ቁጥር ብልጫ የነበራቸው መከላከያዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በኃይሉ ግርማ፣ በምንይሉ እና ማራሊ ወርቁ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ ማራኪ በ53ኛው ደቂቃ ሮበርት ኦዶንካራ የተፋውን ኳስ በቅርብ ርቀት ቢያገኝም ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ የቡርኪናፋሶው አብዱልከሪም ኒኪማ ከአበባው ቡታቆ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ አደርጓል፡፡ በግቡ መቆጠር የተነቃቃቱ ጊዮርጊሶች ሁለተኛ ግብ ለማከል ሶስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር የጠበቁት፡፡ በውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው አበባው አሁንም ከመስመር ያሻገረውን ኳስ አዳነ በግንባሩ በመግጨት ከመረብ አሳርፏል፡፡ የአዳነ ግብ ከጌታነህ ከበደ ጋር የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢ ሰንጠረዥን በጣምራ እንዲመራ አስችሎታል፡፡
መከላከያዎች የነበራቸውን የቁጥር ብልጫ በአግባቡ መጠቀም ያለመቻላቸው እንዲሁም በተከታታይ የተቆጠሩባቸው ሁለት ግቦች ፈፅሞ ከጨዋታው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል፡፡ በ80ኛው ደቂቃ የጦሩ ተከላካይ አዲስ ተስፋዬ ተቀይሮ በገባው ሳላዲን ሰዒድ ላይ በፈፀም ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት እራሱ ሳላዲን መትቶ ሶስተኛውን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ በ85ኛው ደቂቃ ተከላካዩ ሳላዲን ባርጌቾ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ሜዳ ተመልሷል፡፡ ሳላዲን በህዳር 2008 የዲኤስቲቪ ሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ካፕ በመክፈቻ ጨዋታው ኢትዮጵያ በሩዋንዳ 1-0 በተሸነፈችበት ጨዋታ ነበር የጉልበት ጉዳት ያጋጠመው፡፡
በጨዋታው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ስታዲየሚ በአስገራሚ ድባብ ውስጥ እንዲያልፍ አድርገዋል፡፡ የፈረሰኞቹ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ይዘው የመጡት አዲስ የአደጋገፍ ስልት ለስታዲየሙ ድምቀት ሆኗል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
“ቀድመን ጎሎች ማግባታችን ቡድናችን ተነሳሽነቱ እንዲጨምር አድርጓታል” የቅዱስ ጊዮርጊስ ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ
“በመጀመሪያው 45 እንደምንፈልገው አልተጫወትንም፡፡ የዳኛ ፊሽካ ስለበዛብን የጨዋታው እንቅስቃሴ ይቋረጥብን ስለነበር እንደምንፈልገው አላደረግንም፡፡ በሁለተኛው 45 በተጫዋቾች ቁጥር ያነስን ነበርን ግን የተሸለ ለመጫወት ሞክረናል፡፡ ቀድመን ጎሎች ማግባታችን ቡድናችን ተነሳሽነቱ እንዲጨምር አድርጓታል፡፡”
“ስለዳኝነቱ ብዙ ባላወራ ነው ድስ የሚለኝ፡፡ እናንተ አይታችሁታል ዳኘነቱን ለእናንተ እተዋለሁ፡፡ በተቻለ መጠን ቡድናችን ላይ ለማተኮር ሞክረናል፡፡ በሁለተኛው 45 ተጫዋቾቻን እንዲረጋጉ እና እኛ በምፈልገው የጨዋታ እንዲያተኩሩ አድርገናል፡፡”
“ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ነበር አቅደን የመጣነው” የመከላከያ አሰልጣኝ በለጠ ገብረኪዳን
“ጨዋታው ሲጀመር ጥሩ ነበርን፡፡ ኳስ ተቆጣጥረን ለመጫወት ነበር አላማችን ሆኖም ከዕረፍት በኃላ እነሱ ጥሩ ነበሩ፡፡ አራት አጥቂ ነበር ያስገባነው (ከመሃሪ መና የቀይ ካርድ መመልከት በኃላ) ግን ትንሽ ያለመረጋጋት ችግር ነበር፡፡ ማግባት ሲገባን ግብ ተቆጥሮብናል፡፡”
“ጊዮርጊስ ጥሩ ቡድን ነበር፡፡ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ነበር አቅደን የመጣነው፡፡ ከዕረፍት በፊት ጥሩ ነበርን ግብ ከገባብን በኃላ ትንሽ የመረጋጋት ችግር ነበረብን፡፡”