የፕሪሚየር ሊጉ 4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይደረጋሉ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ ይደረጋሉ፡፡ በአሸናፊነት ለመቀጠል እና መጥፎ አጀማመርን ለማስተካከል የሚደረጉ ፍልሚያዎች በ4ኛው ሳምንትም ይቀጥላሉ፡፡

ነገ አንድ ጨዋታ ብቻ ሲደረግ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን ያሰናበተው ደደቢት በአስራት ኃይሌ እየተመራ ሀዋሳ ከተማን 11:30 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ያስተናግዳል፡፡ ደደቢት 4 ፣ ሀዋሳ ከተማ 3 ነጥቦች ይዘው በተቀራራቢ አቋም የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ ጥሩ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እሁድ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ይርጋለም ላይ በ09:00 ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ ሁለቱም እኩል 6 ነጥብ የያዙ ሲሆን ወላይታ ድቻ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገ በኋላ በሁለቱ ቡድኖች መካከል የሚደረገው ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት ሆኗል፡፡

አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና በ09:00 የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላው ተጠባቂ ጨዋታ ነው፡፡ ሁለቱም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ እንደመሆኑ እና አዳማ ለአዲስ አበባ ያላት ቅርበት ጨዋታው ከፍተኛ ቁጥር ባለው ተመልካች እና የሞቀ ድባብ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡

ፋሲል ከተማ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሰን ያስተናግዳል፡፡ ፋሲል ባለፈው ሳምንት ከሜዳው ውጪ ቡናን በማሸነፍ በጥሩ የራስ መተማመን ላይ ሲገኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ በምርጥ አቋም ላይ ይገኛል፡፡

አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ጅማ አባ ቡናን 09፡00 ላይ ያስተናግዳል፡፡ አርባምንጭ ከ3 ጨዋታ 1 ነጥብ ብቻ በመያዝ አስከፊ አጀማመር ያደረገ ሲሆን ጅማ ባለፈው ሳምንት የመጀመርያ የሊግ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል፡፡

መከላከያ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በ09፡00 ወልድያን ያስተናግዳል፡፡ መከላከያ ከ3 ጨዋታ 1 ነጥብ ብቻ ሲያሳካ ወልድያ 5 መሰብሰብ ችሏል፡፡ መከላከያ በዚህ ሳምንት ከዋና አሰልጣኝንት ወደ ረዳትነት አውርዶት የነበረው ምንያምር ጸጋዬ ከዚህኛው ኃላፊነቱም መነሳቱ ተነግሯል፡፡

ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን በ10፡00 ላይ ያስተናግዳል፡፡ አዲስ አበባ በ3 ጨዋታ 5 ነጠብ ሲሰበስብ ድሬዳዋ ከሜዳው ውጪ ያደረጋቸውን 2 ጨዋታዎች ተሸንፎ በሜዳው 3 ነጥብ ማግኘት ችሏል፡፡

የሊጉ 4ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 11፡30 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም በሚያደርጉት ጨዋታ ይጠናቀቃል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች የመጀመርያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይፋለማሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *