ብሔራዊ ቡድኑ ከናይጄርያ ጋር ይጫወታል

ብሔራዊ ቡድኑ ከናይጄርያ ጋር ይጫወታል

በናይጀሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዋና ከተማዋ አቡጃ የፊታችን ታህሳስ 27 ቀን እንዲከናወን የታሰበው ጨዋታ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል ተቀባይነት አግኝቷል።

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወደ አቡጃ ለሚያደርገው ጉዞ የትራንስፖርት ወጭ ብቻ የሚሸፍን ሲሆን ፥ ሌሎች ወጭዎች በናይጀሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አማካኝት የሚሟሉ ይሆናል። ጨዋታው የሚከናወነው የሃገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ በሚካፈሉበት የቻን ውድድር ተሳታፊዎች መካከል ይሆናል። ለብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት ሲባልም ፕሪሚየር ሊጉ ከታህሳስ 20 በኋላ ለ1 ወር ከ15 ቀናት ይቋረጣል። ጥር 3 በደቡብ አፍሪካ ለሚካሄደው 3ኛው የቻን እግር ኳስ ውድድር ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 27 ተጫዋቾችም ዛሬ በፌዴሬሽኑ የጤና ምርመራ ይደረግላቸዋል።

እንደ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቡድኑ ልምምዱን ከታህሳስ 20 በኋላ የሚጀምር ሲሆን ፥ የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን ከወዳጅነት ጨዋታው በኋላ ያሳውቃል ተብሎም ይጠበቃል። በአሰልጣኝ ሰውነት ከተመረጡ 27 ተጫዋቾች አንዱ የሆነው የሲዳማ ቡናው የግራ መስመር ተከላካይ ሞገስ ታደሰ በጉዳት ምክንያት ለጨዋታው እንደማይደርስ ታውቋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሊቢያ ፣ ከጋና እና ከኮንጎ ኪንሻሳ ጋር ተደልድሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ