በሊቢያው ታላቅ ክለብ አል-ኢትሃድ ከአሰልጣኑ ጋር በፈጠረው አለመግባባት ምክንያት በክለቡ ምቾት እንዳልተሰማው ሲነገር የከረመው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ድንቅ አማካይ ሽመልስ በቀለ ሲነገሩ የነበሩ ወሬዎችን ሲያስተባብል ቢቆይም ከ3 ወራት ቆይታ በመጨረሻ የሱዳኑን አል-ሜሪክን ተቀላቅሏል።
ተጫዋቹ ስለ ጉዳዩ ከሰገር ስፖርት ጋር ባደረገው ቆይታ ‹‹ ለአል-ኢትሃድ ለመጫወት ስስማማ የተሻለ ክለብ እና ጥቅማ ጥቅም ካገኘሁ ክለቡን ለመልቀቅ ተስማምቼ ነበር፡፡ አል-ሜሪክ በቻምፒዮንስ ሊጉ የሚካፈል በመሆኑ እና የተሻለ ክፍያ በማቅረቡ ለሜሪክ ፈርሜያለሁ፡፡ ከሱዳኑ ክለብ ጋርም በሊቢያ እንዳደረኩት አይነት ስምምነት ተስማምቻለሁ ›› ሲል ተናግሯል፡፡
በቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሚኬል ክሩገር የሚሰለጥነው አል-ሜሪክ አሰልጣኙ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ተጠቅመው ድንቅ ተጫዋቾችን ለማዘዋወር ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ከሽመልስ ዝውውር ቀደም ብሎ የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት በ5 ግብ እየመራ የሚገኘው ኡመድ ኡኩሪን እና የዋዲ ዴግላውን ኮከብ ሳላዲን ሰኢድ ለማዘዋወር ጥረት እያገረጉ መሆኑ ይታወቃል፡፡
አል-ሜሪክ ሽመልስ በቀለን የ3 አመት ኮንትራት ማስፈረሙ እና ወርሃዊ 5,000 የአሜሪካን ዶላር ለመክፈል ሲስማማ የ3 አመት የኮንትራት ዋጋው 650 ሺህ ዶለር ገደማ መሆኑ ተነግሯል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ