በ4ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡
በአዳማው አበበ ቢቂላ የተካሄደውን ጨዋታ ለመከታተል እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሁለቱም ክለቦች ደጋፊዎች ከ7 ሰአት ጀምሮ ወደ ስታዲየም ሲተሙ ተስተውሏል፡፡ ጨዋታውም በበርካታ የግብ ሙከራዎች እንዲሁም ሽኩቻዎች ታጅቦ ተጠናቋል፡፡
ባለሜዳዎቹ አዳማዎች የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ ለማድረግ የፈጀባቸው 5 ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ ሱሌይማን መሀመድ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪስን እና የአዳማው አጥቂ ሚካኤል ጆርጅ ከተላተሙ በኃላ የተገኘችውን ኳስ ሚካኤል ጆርጅ ቢሞክርም በግቡ አናት በላይ ወጥታለች፡፡
ቡናዎች በ9ኛው ደቂቃ አማኑኤል ዮሀንስ ግብጠባቂው ጃኮብ ፔንዜን አልፎ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ የግቡ አግዳሚ ለትማ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡
በጨዋታው ከታዩ እና መናገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ በ33ኛ ደቂቃ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረው አስቻለው ግርማ ከእለቱ አልቢትር ጋር በፈጠረው እሰጣ ገባ በቀይ ካርድ መሰናበቱ ነበር፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ አካባቢ 37ኛው ደቂቃ ላይ ሳዲቅ ሴቾ ከኤልያስ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል አልፎ የሞኸረው እንዲሁም በ45ኛው ደቂቃ በድጋሚ ሳዲቅ ሞክሮ ጃኮብ ያወጣቸው ኳሶች በኢትዮጵያ ቡና በኩል የሚያስቆጩ ነበሩ፡፡ በተጨማሪው ደቂቃ ላይ ሙጂብ ቃሲም የኤፍሬም ወንደሰንን ስህተት ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ ከግቡ አናት በላይ የሰደዳት ደግሞ በአዳማ በኩል የሚጠቀስ ነበር፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ አክሊሉ ዋለልኝን ተክቶ የገባው ያቡን ዊልያም በ52ኛው ደቂቃ ሳዲቅ ሴቾ የግሉን ጥረት ተጠቅሞ ሁለት ተከላካዮችን በማለፍ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ኢትዮጵያ ቡናን ቡናዎችን መሪ ማድረግ ቻሏል፡፡
ከግቧ መቆጠር በኃላ ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት ቡናዎች በ62ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ ተጨራርፋ የተመለሰችውን ኳስ ሞክሮ ለጥቂት መረቡን ታካ የወጣበት መሪነታቸውን ማስፋት የሚችሉበትን እድል ነበር፡፡
ከግቧ መቆጠር በኃላ አዳማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረግ የጀመሩ ሲሆን በ68ኛው ደቂቃ በፋሲካ አስፋው አማካኝነት ሞክረው ሀሪስን በአስደናቂ ሆኔታ መልሶበታል፡፡ በተመሳሳይ በ71ኛው ደቂቃ ታፈሰ ተስፋዬ ሀሪስን ከግቡ መውጣቱን አይቶ የሞከራትና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችው ኳስ ተጠቃሽ ነበር፡፡
በ80ኛው ደቂቃ ላይ በተለሞዶ ካታንጋ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ጨዋታውን እየተከታተሉ በነበሩ ደጋፊዎች መካከል ግጭት ተቀስቀሶ በተፈጠረው ግርግር እና ወከባ ጥቂት የማይባሉ የኢትዮጲያ ቡና ደጋፊዎች ተጎድተዋል፡፡
በዚህ ግርግር በቀጠለው ጨዋታ በ83ኛው ደቂቃ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ጃኮብ የመታውን ኳስ የኢትዮጵያ ቡና ተከላላካዮች በትኩረት ማነስ የፈጠሩትን ስህተት ተጠቅም ታፈሰ ለሙጂብ ያቀበለውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ወደ ግብነት ቀይሯት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡
ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላ የእለቱ አልቢትር በደጋፊዎች መካከል የተነሳው ግጭት እሲኪበርድ ጨዋታውን ለ4 ያክል ደቂቃዎች እንዲቋረጥ በማዘዛቸው ጨዋታው የተቋረጠ ሲሆን በ90+6ኛው ደቂቃ ላይ ሚካኤል ጆርጅ ከረጅም ርቀት የሞከረው ኳስ ሀሪስተን በግሩም ሆኔታ አድኖት ኢትዮጵያ ቡናን ከሽንፈት ታድጎታል፡፡ ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
” አቻ መውጣታችን መልካም የሚባል ነው” አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ
“እጅግ በርካታ የሚባሉ የግብ እድሎችን አግኝተን ነበር፡፡ ነገር ግን በትኩረት ማጣት ግብ ማስቆጠር አልቻልንም ፤ በዚህ አጋጣሚ ለኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ትልቅ አድናቆቴን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡”
“ሙጂብ ለእኔ ሁለገብ ተጫዋቾች ነው፤ አንድ ተጫዋች ሜዳ የሚገባው ቁጥር ለማሟላት አይደለም ፤ በአሰልጣኙ የተሰጠውን ግዳጅ ለመወጣት እንጂ፡፡ ስለዚህ የተጫዋቹ ትክክለኛ ቦታ የት እንደሆነ ተመልካች የሚፈርደው ነው፡፡ በቀጣይ ከዚህ በተሻለ በቦታው (በአጥቂ ስፍራ) ራሱን እንደሚያሳይ እጠብቃለሁ::”
“ሱራፌል ወደ ፊት ብዙ ደረጃ ይደርሳል ብዬ የምጠብቀው ተጫዋች ነው፡፡ በጥቂት አመታት ውስጥ ሽመልስ በቀለ እና ምንያህል ተሾመን ይተካል ብዬ የምጠብቀው ተጫዋች ነው፡፡”
” ተጫዋቾቼ ባሳዩት እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ” ኒቦሳ ቩሴቪች
“ባለፋት ሶስት ጨዋታዎች እንዳጋጠመን በዛሬውም ጨዋታ ያገኘናቸውን ወደ አራት የሚጠጉ የግብ ማግባት እድሎችን እድለኛ ባለመሆናችን ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል፡፡”
“በሊጉ ካሉት ጠንካራ ቡድኖች አንዱ የሆነውን አዳማን በሜዳው አጥቅተን ተጫውተን ለማሸነፍ ጥረናል ፤ ነገርግን ማሸነፍ አልቻልንም፡፡ በአጠቃላይ ውጤቱ ለኛ ጥሩ የሚባል ነው ፡፡”
“ስለዳኝነቱ ምንም አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም ያገኘናቸው እድሎችን መጠቀም ሳንችል አቻ ወጥተን በዳኝነት ምክንያት ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡”