ከአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ የሴቶች ቡድን መቋቋም ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ውዝግብ ባለፈው ሳምንት እልባት ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ በቀጣዩ ማክሰኞም ክለቡ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን ከሀዋሳ ከተማ ጋር ያደርጋል፡፡ በጉዳዩ ዙርያ ዝምታን መርጦ የቆየው ክለቡ ትላንት በአአ ስፖርት ኮሚሸን ለመጀመርያ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው የተነሱትን ሀሳቦች እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ንጋቱ ዳኛቸው – የቦርድ ጸሃፊ
አዲስ አበባ ከተማ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደጉን ተከትሎ ክለቡ በኢትዮጵያም ሆኘ አፍሪካ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን እና ጠንካራ አደረጃጀት እንዲኖረው የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ ነድፈን ስንንቀሳቀስ ቆይተናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ስንንቀሳቀስ በዋናነት ትኩረት ያደረግነው የወንዶቹን ቡድን አጠናክረን መቀጠል ነበር፡፡ በዚህ አመት የሴቶች ቡድን የመያዝ እቅድ አልነበረንም፡፡ ገና ወደ ፕሪሚየር ሊግ ከመግባታችን እና ማኔጅመንቱም በአዲስ መልክ እየተዋቀረ ከመሆኑ አንፃር በዚህ አመት የሴት ቡድን መያዙ ጫና ይኖረዋል በሚል ከእቅዳችን ውጪ አድርገነው ነበር፡፡ በስትራቴጂክ እቅዳችን ላይ ግን በቀጣይ አመት የማቋቋም እቅድ ነበረን፡፡
ነገር ግን በፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፍ የወንድ ቡድን ስላለን የግድ የሴት ቡድን ሊኖረን ይገባል በሚል አንዳንድ የቦርድ አባላት ከተጠባባቂው ስራ አስኪያጅ ጋር በመሆን ከቦርዱ እውቅና ውጪ የአሰልጣኝ ቅጥር እና የተጫዋቾች ዝውውር በማድረግ የሴቶች ቡድን አቋቁመዋል፡፡ ይህ መንገድ የቦርዱም ሆነ የአስተዳደሩ እውቅና አልነበረውም፡፡ ከፌዴሬሽኑ ደብዳቤ ሲደርሰን ነው ይህ ሁሉ መንገድ እንደተሄደ ያወቅነው፡፡
ከዚህ በኋላ የመጀመርያ ስራችን የነበረው ይህን ድርጊት የፈጸሙ ግለሰቦችን ማንነት የማጣራት ስራ ነበር፡፡ በሌላ በኩል የአሰልጣኞች እና ተጫዋቾች የስራ ፍላጎት እንዲሁም ህጋዊ ነው በሚል መንገድ በዚህ ጉዳይ መሳተፋቸውን ከግምት በማስገባት በጀት ባንይዝም ከፌዴሬሽኑ ጋር ባደረግነው ውይይት ቡድኑን ይዘን እንድንቀጥል ተደርጓል፡፡ ባለፉት 10 ቀናትም ጉዳዩን እልባት ለመስጠት ባደረግነው እንቅስቃሴ ሁሉንም ተጫዋቾች እንዲሁም አሰልጣኙን በሙሉ ተረክበናል፡፡ የሚያስፈልጋቸው ነገሮችን አሟልተን ወደ ስራ እንዲገቡ ያደረግን ሲሆን በቀጣይ ማክሰኞም ቡድናችን በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከሀዋሳ ከተማ የሚያደርገውን ጨዋታ የሚያከናውን ይሆናል፡፡
ቡድኑ ዘላቂነት እንዲኖረው ከአሰልጣኙ ፣ ስራ አስኪያጁ እና ከሁሉም የቡድን አባላት ጋር ውይይት አድርገናል፡፡ አስተዳደሩ በተሻለ ደረጃ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ያደርጋል፡፡ ክለባቸም በእርግጠኝነት የዘንድሮውን ውድድር እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ነን፡፡
ቱቱ በላይ – አምበል
የተፈጠሩትን ችግሮች ሰኞ በነበረው ስብሰባ በመፍታት አስተካክለናል፡፡ ከዚህ ቀደምም በግላችን ልምምድ ስንሰራ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ችግሩ እልባት ካገኘ በኋላ መደበኛ ልምምድ መስራት ጀምረናል፡፡ የሚያስፈልጉን ነገሮች በሙሉ ተሟልተውልናል፡፡ እናም ማክሰኞ ከ ሀዋሳ በምናገርገው ጨዋታ አሸንፈን እንደምንወጣ ተጫዋቾቹን ወክዬ መናገር እፈልጋለሁ፡፡
አስራት አባተ – አሰልጣኝ
እንደባለሙያ ከፊታችን ላለው ጨዋታ በስነ ልቦናው ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ከቦርዱ ጋርም በጉዳዩ ዙርያ ግልጽ ውይይት አድርገናል፡፡ ዋናው ነገር የተሻለ አዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ቡድንን መፍጠር እንደሆነ ከውሳኔ ደርሰናል፡፡ ባለፉት ሶስት ቀናትም ያለፈውን ረስተን ስለወደፊቱ ነው እያሰብን ያለነው፡፡