የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ዛሬ እና ነገ ይደረጋሉ፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም 2 ጨዋታዎች ሲካሄዱ ነገ 6 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
የዛሬ ጨዋታዎች
ኢትዮ ኤሌክትሪክ አርባምንጭ ከተማን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ዛሬ በ09:00 የሚያስተናግድበት ጨዋታ የሳምንቱ ቀዳሚ መርሃ ግብር ነው፡፡ አርባምንጭ ባለፈው ሳምንት ጅማ አባ ቡና ላይ የውድድር ዘመኑን መጀመርያ ድል በማስመዝገብ የተነቃቃ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ የመጀመርያ 3 ነጥቡን ለማሳካት አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ ባለፈው ሳምንት ቡድናቸውን ያልመሩት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጸጋዬ ዛሬ ወደ መቀመጫቸው ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
11:30 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና ይፋለማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ከመጥፎ አጀማመሩ ለማገገም ፤ በ9 ነጥብ 2 ደረጃ ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድል ለማስመዝገብ ይጫወታሉ፡፡ አስቻለው ግርማ በቅጣት የማይሰለፍ ሲሆን አንተነህ ተስፋዬ በጉዳት የመሰለፍ እድሉ አጠራጣሪ ነው፡፡
የነገ ጨዋታዎች
መልካ ቆሌ ላይ በአማራ ደርቢ ወልድያ ፋሲል ከተማን 09:00 ላይ ያስተናግዳል፡፡ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት 1 ብቻ በመሆኑ ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ለህክምና ወደ ባንኮክ በማምራቱ ፋሲል የነገውን ጨዋታ የሚያደርገው በረዳት አሰልጣኙ መሪነት ይሆናል፡፡
አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አዲስ አበባ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 09:00 ላይ ይጫወታሉ፡፡ ጨዋታው አዲስ አበባ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ንግድ ባንክ የመጀመርያ ድሉን ለማስመዝገብ የሚደረግ ጨዋታ በመሆኑ ለሁለቱም አስፈላጊ ነው፡፡ በአአ ከተማ በኩል ተከላካዮቹ አልሳዲቅ አልማሂ እና ዳንኤል አባተ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆን በቡድኑ የኋላ መስመር ላይ መሳሳትን ፈጥሯል፡፡
ጅማ አባ ቡና ደደቢትን ጅማ ላይ በ09:00 ያስተናግዳል፡፡ አዲሱ የደደቢት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ፈተናቸውን ከአርባምንጭ በሽንፈት ከተመለሰው ጅማ አባ ቡና ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ የሚጀምሩ ይሆናል፡፡ በጅማ አባ ቡና በኩል በጉልበት ጉዳት እስካሁን ጨዋታ ማድረግ ካልቻለው ቢንያም አሰፋ ውጪ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ የሆነ ተጫዋች የለም፡፡ ደደቢትም በተሟላ ቡድን ወደ ጅማ አምርቷል፡፡
ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ድሬዳዋ ከተማን 09:00 ላይ ይገጥማል፡፡ ድቻ ተከታታይ 3ኛ የሜዳ ጨዋታውን በድል ለመወጣት ፤ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ አምና ቦዲቲ ላይ ያስመዘገበውን ድል ለመድገም ይፋለማሉ፡፡ አሰልጣኝ መሳየ ተፈሪ የተጫዋቻቸውን ሚና በመለዋወጥ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ሲጠበቅ ድሬዳዋ ከተማ ቅጣት ላይ ከሚገኘው ተስፋዬ ዲባባ ውጪ የተሟላ ቡድን ይዞ ወደ ሶዶ አምርቷል፡፡
ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ መከላከያን 09:00 ላይ ያስተናግዳል፡፡ መከላከያ ባለፈው ሳምንት የመጀመርያ 3 ነጥቡን ሲያገኝ ሀዋሳ አዲስ አበባ ላይ በደደቢት ተሸንፏል፡፡ በሁለቱም በኩል የተመዘገበ አዲስ የተጫዋቾች ጉዳት የሌለ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ በፊት መስመር ያቸውን ክፍተት ለመድፈን ጠንካራ ልምምድ እያደረገ እንደሆነ ታውቋል፡፡
በ5ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ 11:30 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች አንዱ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሽንፈት ፣ አዳማ ከተማ ከአቻ ውጤት በኋላ የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ አስቻለው ታመነ የ4 ጨዋታ ቅጣቱን ጨርሶ ወደ ሜዳ ሲመለስ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የገተመዘጠበ ጉዳት የለም፡፡
በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና በእኩል 9 ነጥብ በግብ ልዩነት ተበላልጠው አናት ላይ ሲቀመጡ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ በ5 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ይመራል፡፡