የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ እና ይርጋለም በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡
በ9 ሰአት ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና የአምናው ሻምፒዮን ደደቢትን በሚያሰተናግድበት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ከወራጅ ቀጠና ለማምለጥ ደደቢትም ከዋንጫ ፉክክሩ ላለመራቅ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በ13 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሲዳማ ቡና ዛሬ የ1ኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታውን የሚያደርግ ሲሆን ካሸነፈ ደረጃውን በእጅጉ የማሻሻል እድል አለው፡፡ደደቢት ባለፈው ማክሰኞ በኢትዮጵያ ቡና ከተሸነፈ በኋላ ለዋንጫው የሚያደርገው ጉዞ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቷል፡፡ 4 ቀሪ ጨዋታ እያለው በ15 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ቢገኝም ጨዋታዎችን ለማሸነፍ የሚቸገር ቡድን ሆኗል፡፡
የደደቢት አጥቂዎች የሆኑት ሚካኤል ጆርጅ እና አሸናፊ አደም በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ሲዳማ ቡናን ከለቀቁ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ይርጋለም የሚጓዙ ሲሆን ከሴፋክሲያን ጋር በተደረገው ጨዋታ ጉዳት የደረሰበት ሚካኤል ዛሬ የመሰለፍ እድል ጠባብ ነው፡፡
በ11፡30 የሚካሄደው የኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከነማ ከቡድኖቹ ትልቅነት እና ለዋንጫ ከሚያደርጉት ፉክክር አንፃር የሚጠበቅ ጨዋታ ነው፡፡ የደደቢቱን ጨዋታ ጨምሮ 4 ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎችን ያሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ ካሸነፈ በ25 ነጥብ ነገ ጨዋታ የሚያደርገው ንግድ ባንክን ቀድሞ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ሲሆን ሀዋሳ ከነማ በበኩሉ ጨዋታን ካሸነፈ ነጥቡን ወደ 18 ነጥብ ያደርሳል፡፡
ለኢትዮጵያ ቡና ለ8 አመታት የተጫወተውና በቢጫው ማልያ ከ100 ግቦች በላይ ግብ ያስቆጠረው ታፈሰ ተስፋዬ ኢትዮጵያ ቡናን ለቆ በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ሀዋሳ ከነማን ከተቀላቀለ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ ቡናን በተቃራኒነት የሚገጥም ሲሆን ከቡና ደጋፊዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ይደረግለታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና በኩል ጀማል ጣሰው ፣ ሚልዮን በየነ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ከሀዋሳ ከነማ በኩል ደግሞ የመሃል ተከላካዩ ግርማ በቀለ በጉዳት አይሰለፉም፡፡
{jcomments on}