የ13ኛው ሳምንት መርሃ ግብሩን በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ምክንያት የተራዘመበት ደደቢት አርብ ምሽት ከመብራት ኃይል ጋር ባደረገው ተስተካካይ ጨዋታ በድራማዊ ትእይንቶች ታጅቦ 4-2 አሸንፎ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡
ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት መብራት ኃይሎች ነበሩ፡፡ በ4ኛው ደቂቃ ከበረከት ይስሃቅ የተሸገረለትን ግሩም ኳስ ተጠቅሞ ራምኬ ሎክ መብራት ኃይልን መሪ የምታደርግ ግብ ኣስቆጥሯል፡፡ በ18ኛው ደቂቃ ደደቢት በድንቅ አማካዩ ታደለ መንገሻ ግሩም ግብ አቻ መሆን ቢችሉም መብራት ኃይል አብዱልከሪም ሃሰን ባስቆጠራት ግብ በድጋሚ ወደ መሪነት ተመልሷል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ የተጠናቀቀውም በመብራት ኃይል 2-1 መሪነት ነው፡፡
በ2ኛው አጋማሽ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርግ መብራት ኃይሎች በበኩላቸው በጥልቀት በማፈግፈግ መከላከልን መርጠዋል፡፡ ይህ የመብራት ኃይል መከላከል እስከ 83ኛው ደቂቃ ድረስ ዘልቆ ውጤቱን ላስጠበቅ ጥረት ቢያደርጉም የታደለ መንገሻ ግሩም ግብ ሁሉንም ነገር አበላሽቶባቸዋል፡፡
በ89ኛው ደቂቃ ሽመክት ጉግሳ ተጨማሪ ግብ አክሎ ደደቢት ወደ መሪነት ሲቀይረው በ91ኛው ደቂቃ የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ታደለ መንገሻ ወደ ግብ ቀይሮ በመጨረሻም በደደቢት 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ደደቢት ይህንን ጨዋታ ማሸነፉን ተከትሎ 5 ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ15 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
{jcomments on}