ወላይታ ድቻ የገቢ ማሰባሰብያ ሩጫ ውድድር ያካሂዳል

የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ራሱን በገቢ ለማጠናከር  በማሰብ የሩጫ ውድድር አዘጋጅቷል፡፡

በ2006 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከተቀላቀለ ወዲህ በአነስተኛ ወጪ በሊጉ ተፎካካሪ መሆን የቻለው ወላይታ ድቻ ክለቡን ለማጠናከር የፊታችን ታህሳስ 15 በወላይታ ሶዶ ከተማ 15ሺህዝብ የሚሳተፍበት የአምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ያከናውናል፡፡ በርካታ ደጋፊ ያለው ድቻ ውድድሩን ያዘጋጀበት አላማ የክለቡን ህዝባዊነት ከድጋፍ ባለፈ ወደ ገንዘብ ለመለወጥ በማለም መሆኑን ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡

ወላይታ ድቻን በገንዘብ እንዲሁም በቁሳቁስ  15 ሺህ አርሶአደሮች ፣ 20ሺህ የመንግሥት ሰራተኞች ፣ 12 ባለሀብቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የክለቡ ወዳጆች ድጋፍ እንደሚደረግለትም ተገልጿል፡፡ ክለቡ ባሳለፍነው መስከረም ከሲዳማ ቡና እና ኢትዮጰያ ቡና ጋር የወዳጅነት ጨወታዎችን በማድረግ ለወላጅ አልባ ህጻናት እርዳታ ማዋሉ ይታወሳል፡፡

ክለቦች ለገቢ ማሰባሰብያ የሩጫ ውድድር ሲያደርጉ ይህ የመጀመርያ ጊዜ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ማዘጋጀታቸውም ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *