ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አይዛክ ኢዚንዴ ተለያይተዋል

ዩጋንዳዊው የመሃል ተከለካይ አይዛክ ኢዜንዴ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተለያይቷል፡፡ የውል ዘመኑ ያበቃው አይዛክ ከፈረሰኞቹ ቤት ለቆ ወደ ትውልድ ሃገሩ ተመልሷል፡፡

በ2003 የውድድር ዘመን አጋማሽ በሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ካፕ ባሳየው አቋም ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ተጨዋቹ በአሰልጣኝ ማርት ኖይ ስብስብ ውስጥ ቦታ ለማግኘት በ2009 የውድድር ዓመት ሲቸገር ተስተውሏል፡፡ የመሃል ተከላካዮቹ ደጉ ደበበ እና አስቻለው ታመነ በጉዳት እና ቅጣት ባልነበሩበት ጨዋታ ቋሚ ሆኖ መሰለፍ ቢችልም ከክለቡ የመልቀቁ ነገር ግን የሰፋ ነበር፡፡

የዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቾ በመጪው ሰኞ ክሬንሶቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅታቸውን ሲጀምሩ አይዛክን እንደሚያካቱት ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ ሚቾ ዩጋንዳ በአፍሪካ ዋንጫ እንዲሁም በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ያደረገቻቸውን ጨዋታዎች አይዛክን በቋሚነት የተጠቀሙ ሲሆን ለብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ ከሆኑት ተጫዋቾች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በመሃል ተከላካይ ቦታ አራት አማራጮች አሉት፡፡ ከጉዳት የተመለሰው ሳላዲን ባርጌቼን ጨምሮ ምንትስኖት አዳነ፣ ደጉ ደበበ እና አስቻለው ታመነ የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *