የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች በነገው እለት ይካሄዳሉ፡፡
ይርጋለም ስታድየም ላይ ሲዳማ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ በዚህ ሳምንት ከሚካሄዱ ጨዋታዎች ተጠባቂው ነው፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በ1 ነጥብ ብቻ ተበላልጠው በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የሚገኙ መሆናቸው ጨዋታውን ፈታኝ ያደርገዋል፡፡
በሲዳማ ቡና በኩል በልምምድ ወቅት ባጋጠመው ጉዳት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ ያልተሰለፈው በረከት አዲሱ ወደ ጨዋታ ሲመለስ አንተነህ ተስፋዬ ከጉዳቱ አገግሞ የመሰለፉ ጉዳይ አጠረጣሪ ነው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ መሀሪ መናን በቅጣት የሚያጣ ሲሆን ምንያህል ተሾመ በጉዳት ከቡዱኑ ጋር ወደ ይርጋለም አልተጓዘም፡፡ ወጣቱ ፍሬዘር ካሳ ደግሞ ከጉዳቱ አገግሞ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል፡፡
ወላይታ ድቻ በሜዳው ሶዶ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡናን የሚጋብዝበት ጨዋታ ሌላው ትኩረት ከተቸራቸው ጨዋታዎች መካከል ነው፡፡ ድቻ በሜዳው ያለው ጥንካሬ ባለፈው ሳምንት የመጀመርያ ድሉን ላጣጣመው ኢትዮጵያ ቡና ፈተና ይሆናል፡፡
ድቻ ጠንካራው ተከላካይ ፈቱዲን ጀማልን በጉዳት ሲያጣ ሌሎቹ ከጉዳት ነፃ ሆነው ጨዋታውን ይጠባበቀሉ። ቡና የአምበሉ መስኡድ መሀመድ ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና ዮሐንስ በዛብህን ግልጋሎት በጉዳት ሲያጣ አስቻለው ግርማም በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል፡፡
ፋሲል ከተማ ሀዋሳ ከተማን ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ያስተናግዳል፡፡ የአሰልጣኝ ዘማርያምን መራሪነት በህክምና ምክንያት የማያገኘው ፋሲል ከጉዳት ነፃ በሆነ ቡድን ሀዋሳን ሲገጥም ሀዋሳ ጋዲሳ መብራቴ ፣ አዲስ አለም ተስፋዬ እና ዳንኤል ደርቤን በቅጣት አያሰልፍም፡፡
ኤሌክትሪክ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል ለማግኘት በማለም ደደቢትን ይገጥማል፡፡ በ2001 ኤሌክትሪክን ያሰለጠኑት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌም የቀድሞ ክለባቸውን ይገጥማሉ፡፡
በደደቢት በኩል መጠነኛ ጉዳት የነበረባቸው ጌታነህ ከበደ እና ሽመክት ጉግሳ አገግመው ለጨዋታው ብቁ ሲሆኑ ኤሌክትሪክ ዳዊት እስጢፋኖስ እና በረከት ተሰማን በጉዳት ያጣል፡፡
አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ አዲስ አበቢ ከተማን ያስተናግዳል፡፡ አርባምንጭ ከጉዳት ነፃ ስብስብ ይዞ የመዲናውን ክለብ ሲገጥም ሁሉም በአአ በኩል ተክለማርያም ሻንቆ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ያለፈው ጨዋታ ያመለጣቸው አልሳዲቅ አልማሂ እና ዳንኤል አባተም እንዲሁ የነገው ጨዋታ የሚያመልጣቸው ተጨዋቾች ናቸው፡፡
ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ኢተዮጵያ ንግድ ባንክን ይገጥማል፡፡ በሁለቱም በኩል የተመዘገበ የጉዳት ዜነና የሌለ ሲሆን በሙሉ ስብስባቸው ይፋለማሉ፡፡
አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ አዳማ ከተማ ወልድያን ይገጥማል፡፡ በአዳማ ከተማ በኩል ምንም ጉዳት ያልተመዘገበ ሲሆን የወልድያ ተጫዋቾችም በተመሳሳይ ከጉዳት ነፃ ናቸው፡፡ በጉዳት ያለፈው ጨዋታ ያመለጠው ዳንኤል ደምሴም ለጨዋታው ብቁ ሆኗል፡፡
አዲስ አበባ ስታድየም ላይ መከላከያ ከጅማ አባ ቡና 11:30 ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ የ6ኛው ሳምንት ማሳረጊያ ይሆናል፡፡ በመከላከያ በሀዋሳው ጨዋታ ላይ ቀይ ከተመለከተው ታፈሰ ሰርካ ውጭ ሁሉም ዝግጁ ሲሆኑ በጅማ አባቡና በኩልም የተመዘገበ አዲስ ጉዳት እና ቅጣት የለም፡፡