የጨዋታ ሪፖርት | መከላከያ 1-0 ጅማ አባ ቡና

የስድስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማገባደጃ መርሀ ግብር 11: 45 ላይ መከላከያን ከጅማ አባ ቡና አገናኝቶ ጦሩ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል ።

ቀዝቀዝ ባለ አየር እና በቀኝ ከማን አንሼ በኩል በዛ ብለው ጨዋታውን ሲያደምቁ በነበሩት የእንግዳው ቡድን ጅማ አባ ቡና ደጋፊዎች ሞቅ ያለ ዝማሬ የተጀመረው የሁለቱ ብድኖች ፉክክር የመጀመሪያ አጋማሽ ያለግብ ተጠናቋል። ተመሳሳይ የጨዋታ ቅርፅ የነበራቸው ሁለቱ ቡድኖች እምብዛም ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ ባያሳዩም ተመጣጣኝ የሆኑ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል።

ጨዋታው በተጀመረ በ11ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ታዬ ከመሀል የጣለለትን ማራኪ ወርቁ ወደግብ ከመሞከሩ በፊት ጀማል ጣሰው ደርሶ ያወጣበት ኳስ የባለሜዳው ቡድን የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። በ17ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሚካኤል ደስታ ወደ ግራ  የሰነጠቀለትን የግራ መስመር ተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለ ወደውስጥ የመታት ኳስ ጀማል ጣሰውን ካለፈችው በኃላ የግራ መስመር ተከላካዩ ጀሚል ያዕቆብ ከግቡ ቋሚ ስር አውጥቷታል።

የባለሜዳዎቹ የተከላካይ አማካይ በሀይሉ ግርማ በበኩሉ በ22ኛው ደቂቃ ከጅማዎች ሳጥን ግራ ጠርዝ ላይ የተገኘችውን ቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ ጀማል ጣሰው አውጥቶበታል። ከነዚህ ውጪ በ35ኛው ደቂቃ ላይ መከላካዮች ያገኙትን የማእዘን ምት ሽመልስ ተገኝ አሻምቶት ሚካኤል ግርማ በግንባሩ ሞክሮ የወጣበትም የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

ከፊት በአሜ መሀመድ መሀል ላይ ደግሞ በ ክርቶፈር ንታንቢ የግል ብቃት ታጅበው መጀመሪያውን ግማሽ ጥሩ የተንቀሳቀሱት ጅማ አባ ቡናዎችም በበኩላቸው በ12ኛው ደቂቃ መሀመድ ናስር ከግራ መስመር የተገኘውን እጅ ውርወራ ተጠቅሞ በግንባሩ በሞከረው እና ወደላይ በወጣበት ኳስ ነበር የባለሜዳዎቹን ግብ መፈተሽ የጀመሩት። በ27ኛው ደቂቃ ላይም መሀመድ ናስር በግራ በኩል ከአሜ መሀመድ የተሻገረለትን ኳስ ይዞ ወደመከላለያ ግብ በሚሄድበት ሰዐት በቴውድሮስ በቀለ ጥፋት ተሰርቶበት የተሰጠውን ቅጣት ምት ራሱ መሀመድ ናስር መቶ ወደ ውጪ ሰዶታል። ከዚህ ቅጣት ምት በኃላም የተለመደው የዳኛና የተጨዋቾች ውዝግብ ተነስቶ ቴዎድሮስ በቀለ በጥፋቱ እንዲሁም ሳሙኤል ታዬ በውዝግቡ ምክንያት የቢጫ ካርድ ማስጠንቀቂያ ተመልክተዋል።

ከሁሉም ሙከራዎች በላይ ለጅማ አባ ቡናዎች የምታስቆጭ የነበረችው አጋጣሚ ግን 40ኛው ደቂቃ አካባቢ አሜ መሀመድ ከ ዳዊት ተፈራ የተቀበለውን እና ለ መሀመድ ናስር ያሻማለትን ኳስ መሀመድ ከተቆጣጠራት በኃላ በአግባቡ ሳይሞክር የመለላላከያ ተከላካዮች ተደርበው ባወጡበት አጋጣሚ የታየች ነበረች።

ሁለተኛው ግማሽ በመከላካዮች ኳስን ይዞ በመጫወት ወደጎል በመጠጋት እና ግብ ለማግኘት በመሞከር እንዲሁም በጅማዎች በአሜ መሀመድ የሚመራ ፈጣን መልሶ ማጥቃት ነበር የተጀመረው።  የመጀመሪያው ሙከራም በ48ኛው ደቂቃ በግምት ከ35 ሜትር ርቀት ላይ መከላካዮች ያገኙትን ቅጣት ምት አዲሱ ተስፋዬ በቀጥታ አክርሮ መትቶ ጀማል ጣሰው አውጥቶበታል፡፡

በ54ኛው ደቂቃም  ማራኪ ወርቁ ከጅማ የመከላከል ሳጥን ውስጥ የመታው ኳስ የግቡን የጎን መረብ ታኮ ወጥቷል።

በጅማዎች በኩል አስገራሚ እንቅስቃሴ ሲያረግ ከነበረው አሜ መሀመድ በ57 እና 58ኛው ደቂቃ የተነሱ ኳሶች በመሀመድ ናስር እና በ ዳዊት ተፈራ አማካይነት ተሞክረው ሁለቱም በመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ ድንቅ ብቃት ተመልሰዋል።

ከነዚህ ሙከራዎች በኃላ ጨዋታው ቀጥሎ በ70ኛው ደቂቃ ላይ የእለቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ተከስትቷል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ የስታድየሙ ፓውዛ ሳይታሰብ በግማሽ ጠፍቶ ጨዋታው እንዲቋረጥ አስገድዷል። ከ25 ደቂቃዎች ጥበቃ በኃላ የፓውዛው መብራት ሲመለስ በሚካኤል ደስታ የመሀል ሜዳ ቅጣት ምት ጨዋታው ሲጀመር ቅጣት ምቱ ተመቶ ተጨርፎ ሲወጣ የተሰጠውን የማእዘን ምት ቴዎድሮስ በቀለ በግንባሩ በመግጨት ሞክሮ ለጥቂት ወደላይ ወጥቶበታል።

በ78ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ የተሻማውን ኳስ የጅማ አባ ቡና ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ጀማል በአግባቡ ከግብ ክልላቸው ሳያርቁት ቀርተው ቴዎድሮስ በቀለ አግኝቶ የቡድኑን የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል።

በ60ኛው ደቂቃ መስፍን ኪዳኔን ተክቶ ወደሜዳ የገባው ሳሙኤል ሳሊሶ በ84ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት በግቡ የቀኝ ቋሚ የወጣበት ሙከራ የመከላከያዎች ምርጡ ሙከራ ነበር ማለት ይቻላል። በ89ኛው ደቂቃ ላይም ሳሙኤል ሳሊሶ ከዛው ከግራ መስመር አሻምቶ አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ በግንባር ሲገጫት የግቡን ቋሚ ለትማ የወጣችበት አጋጣሚም ሌላው ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል ለመሆን የተቃረበች ሙከራ ነበረች። ከመብራቱ መመለስ በኃላ ወደጨዋታው መንፈስ በቶሎ መመለስ ያልቻሉት ጅማ አባ ቡናዎችም የአቻነት ግብ ሳያስቆጥሩ የእለቱ ፍልሚያ በመከላካዮች የበላይነት ተጠናቋል።

ጨዋታው የጅማ አባ ቡና አጥቂዎች በተደጋጋሚ የመከላከያዎች የጨዋታ ውጪ ወጥመድ ሰለባ ሲሆኑ ሲያሳየን ከጅማ አባ ቡና አጥቂው አሜ መሀመድ ከመከላከያ ደግሞ ቴዎድሮስ በቀለ እና ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ጥሩ እንቅስቃሴ ያረጉበት ሆኖ አልፏል ።

የአሰልጣኞች አስተያየት

picsart_1482088133678

በለጠ ገብረኪዳን – መከላከያ

” የጨዋታው እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ቡድናችን አሸንፏል ፤ ከጊዜ ወደጊዜም ወደጥሩ ነገር እየመጣን ነው ከማሸነፋችንም ባሻገር እንቅስቃሴያችን እና ልጆቹ ላይ የነበረው ፍላጎት ጥሩ ነበር። ብዙ እድል እንደመፍጠራችን ከዚህም በላይ ማግባት እንችል ነበር፡፡ ስለዚህ በውጤቱም በጨዋታውም በጣም ደስተኛ ነኝ ”

” እግር ኳስ ጨዋታ የግል ጨዋታ አይደለም፡፡ ቡድን ጥሩ ሲሆን ነው ማሸነፍ የሚቻለው አጥቂ ጎል ቢያገባም እግር ኳስ ሒደት ነው፡፡ ስለዚህ በግል ሳይሆን ቡድኑ እንደቡድን በነበረው እንቅስቃሴ እና በልጆቼ የጨዋታ ፍላጎት በጣም ተደስቻለው። ”

picsart_1482088170846

ደረጄ በላይ – ጅማ አባ ቡና

“ግብ ጠባቂያቸው ሁለት ያለቀላቸውን ኳሶች አድንኗል እንጂ የተሻለን ነበርን አጥቂዎቻችንም የሚችሉትን ሞክረዋል ነገር ግን አቤል ጥሩ ነበር ።”

” ጨዋታው 30 ደቂቃ ከጠበቅን በኃላ መቋረጥ ነበረበት መቀጠሉ አልተመቸኝም፡፡ ነበር ፤ ህግ ከሆነ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም። ”

” በልጆቼ በጣም ተደስቻለው ከሜዳችን ውጪ ብንጫወትም ሜዳችን ላይ ምንጫወት ነበር ሚመስለው ።”

” ጀማል በጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ ብዙ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችንም አድኖ ነበር፡፡ እንደ እድል ሆኖ አንድ ስህተት ሰርቷል ። እግር ኳስ የስህተቶች ጥርቅም ነው፡፡ ግን ሽንፈቱ ያስቆጫል ቡድናችን መሽነፍ አልነበረበትም ። በቀጣይ ጨዋታ በሜዳችን ወደአሸናፊነት እንመለሳለን። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *