የፋሲል ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በታይላንድ ባንኮክ ያደረገውን ህክምና አጠናቆ ትላንት ወደ ሀገርቤት ተመልሷል፡፡
ዘማርያም ስለ ህክምናው እና ተያያዥ ጉዳዮች ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት የተሳካ ህክምና አድርጎ መመለሱን ተናግሯል፡፡
” በመጀመርያ ባንኮክ ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል አምርቼ የተወሰኑ ቀናት በመቆየት የMRI ምርመራ ካደረጉልኝ በኋላ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነና ህክምናውን እንደማያደርጉልኝ ሲገልፅልኝ ባንቦግራድ ሆስፒታል ወደሚገኝ የታወቀ ፕሮፌሰር በማምራት በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቄያለሁ፡፡ ምናልባት በህመሙ ባህርይ ምክንያት ተመልሶ ሊመጣ የሚችል ቢሆንም 85% ሰኬታማ ህክምና እንደተደረገልኝ የህክምና ባለሙያው ገልፆልኛል፡፡ ምናልባት ሕመሙ ተመልሶ የሚመጣ ከሆነ ከ3 ወር በኋላ ለድጋሚ ምርመራ የማቀና ይሆናል፡፡ ” ብሏል፡፡
ፋሲል ከተማ ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ካለ አሰልጣኝ ዘማርያም የተጫወተ ሲሆን በመጪው እሁድ ፋሲል ወደ ጅማ ተጉዞ ጅማ አባ ቡናን በሚገጥምበት ጨዋታ ላይ ቡድኑን ይመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
” እሁድ ከጅማ አባቡና ጋር ጅማ ላይ ጨዋታ አለን፡፡ እንደሚታወቀው ኦፕሬሽን ካደረኩ ገና አራት ቀን ነው፡፡ ነገር ግን የጤናዬ ሁኔታ ካልገደበኝ በቀር በክራንችም ቆሜ ቢሆን ክለቤን የምመራ ይሆናል” ሲል ቡድኑን ተመልሶ ለመምራት ያለውን ጉጉት ገልጿል፡፡
በመጨረሻም አሰልጣኝ ዘማርያም በፍጥነት የውጭ ሀገር ህክምና አድርጎ እንዲመለስ ላገዙት የፋሲል ደጋፊዎች እና ተጫዋቾች ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
” የፋሲል ደጋፊን መቼም አመስግነኸው የማትጨርሰው ቢሆንም ለእነሱ የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለው። በተለይ ግን ተጨዋቾቼ ከስምንት መቶ ሠላሳ ሺህ ብር ያላነሰ ገንዘብ ነው አዋጥተው የሰጡኝ፡፡ ለነሱም ያለኝን አክብሮት እገልፃለው፡፡ በአጠቃላይ በተለያዩ መንገዶች አብሮነታቸውን በመግለፅ ከጎኔ በመሆን ለደገፉኝ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለው። ” ሲል አስተያየቱን አጠቃሏል፡፡