ሮበርት ኦዶንካራ ስለ ዩጋንዳ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ይናገራል

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ዩጋንዳዊ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ሃገሩ ከ39 ዓመታት በኃላ ማለፍ ወደ ቻለችበት የአፍሪካ ዋንጫ ስትመለስ ከሚወክሏት መካከል አንዱ ነው፡፡ የአምስት ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ የሆነው ኦዶንካራ አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቾ በሚመራው ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ቦታ ለማግኘት አልተቸገረም፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ተጫዋቹን ባሳለፍነው ሳምንት ስለአፍሪካ ዋንጫው ዝግጅት አናግራ እንደሚከተለው አሰናድታለች፡፡

ስለዝግጅት

“እውነት ለመናገር ወደ የዋንጫ ውድድር ስትመጣ ብዙም ተነሳሽነት አትፈልግም፡፡ ራስህን ከማነሳሳት ባሻገር ትኩረት ሰጥተህ ስራህን በመስራት ለተሻለ እድል መንገድ ትጠርጋለህ፡፡ ከቡድኔ ጋርም በግልም በጣም እየሰራሁ ነበር፡፡ ውድድሩን በጉጉት እየጠበኩ ነው፡፡ እድሉ ከተሰጠኝ ድግሞ መጠቀም አለብኝ፡፡”

ክሬንሶቹ ስለሚገኙበት ጠንካራ ምድብ

“ዩጋንዳ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣት ሃገር ሆኗ ነው ወደ ውድድር የምትገባው፡፡ ሁሌም በቡድን ነው የምንጫወተው ፤ የተለየ የምንለው ተጫዋች የለም፡፡ አውቃለው ሰዎች ዝቅ አድርገው እንደሚመለከቱን ግን በውድድር የሚከሰተው አይታወቅም፡፡ በውድድሩ የሚቻለንን አድርገን ከምድቡ ለማለፍ ነው የምንሞክረው፡፡ ”

ስለዩጋንዳ ግብ ጠባቂዎች

“ባለፉት ዘመናት በዩጋንዳ የግብ ጠባቂዎች ችግር ነበር፡፡ ቢሆንም ጥሩ ጥሩ የሆኑ ግብ ጠባቂዎችን ዩጋንዳ ማፍራት ችላለች፡፡ አውነት ለመናገር ለእኛ ይህ በራስ መተማመናችንን ይጨምራል፡፡ ብዙዎቹ ከሃገር ውጪ የሄዱ ግብ ጠባቂዎች የተሻለ ብቃት አሳይተዋል፡፡ ለብሄራዊ ቡድን ለመመረጥ ያለው ፉክክር በራሱ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ ማንም በቦታው ቢኖር ዩጋንዳን ስለሚወክል የተሻለ ነገር መስራት አለበት፡፡ ጠንካራ ዝግጅት ካደረግህ ከዛ በኃላ ያለው ውሳኔ የአሰልጣኙ ነው፡፡”

ስለብሄራዊ ቡድን አሰልጣኙ

“ሚቾ ጠንካራ ሰራተኛ ነው፡፡ ተጫዋች የሚመርጠው በወቅታዊ ብቃት እንጂ በጓደኝነት አይደለም፡፡ ለዩጋንዳ እግርኳስ ብዙ ነገር ሰርቷል፡፡ ከሃገሪቱ ብዙ ተጫዋቾች እንዲወጡ አድርጓል፡፡ ለዚህም እውቅና ልንሰጠው ይገባል፡፡ አሁንም ወደ ፊት እንድንጓዝ እያደረገን ነው፡፡ ያለሱ አሁን ያለንበት ደረጃ ላንደርስ እንችላለን፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *