በ2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው ወልዲያ ስፖርት ክለብ በድሩ ኑርሁሴን በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ 1-0 ማሸነፍ ችሏል።
በቅርቡ ግንባታው ወደተጠናቀቀው እና ጥር 6 የሚመረቀው ዘመናዊው ሼህ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲ ስታዲየም የሚዘዋወሩት ወልዲያዎች በመልካቆሌ ስታዲየም ለመጨረሻ ጊዜ ባደረጉት ጨዋታ ግብ ለማስቆጠር የሰከንዶች ጊዜ ብቻ ፈጅቶባቸዋል። ጨዋታው እንደተጀመረ ሀብታሙ ሸዋለም ወደ አደጋ ክልሉ ያሻገረውን ኳስ በድሩ ኑርሁሴን ከተቆጣጠረ በኋላ በጥሩ አጨራረስ ግብ አስቆጥሮ ወልዲያን መሪ አድርጓል። ግቡም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2009 ዓ.ም. የውድድር ዘመን የተቆጠረ ፈጣኑ ግብ በመሆን ተመዝግቧል።
ወልድያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ወደግብ በመድረስ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በአንዱአለም ንጉሤ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ፣ ምንያህል ይመር እና ሀብታሙ ሸዋለም አማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። የኢትዮጵያ ቡናው አሠልጣኝ ኒቦሳ ቩሴቪች በ30ኛው ደቂቃ አማኑኤል ዮሐንስን አስወጥተው ሳሙኤል ሳኑሚን ወደሜዳ በማስገባት ያላቸውን የማጥቃት አማራጭ ለማስፋት ቢሞክሩም ቡድናቸው አህመድ ረሺድ በግራ መስመር በኩል ኳሱን ይዞ ወደሳጥኑ ውስጥ በመግባት መትቶ የወልዲያው ግብ ጠባቂ ኤሜክሪል ቢሊንጌ ከያዘበት ሙከራ ውጪ የሚጠቀስ የግብ አጋጣሚ መፍጠር አልቻለም ነበር።
በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ኢትዮጵያ ቡና አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ ለማግኘት የተሻለ የተንቀሳቀሱ ሲሆን በአንፃሩ ወልዲያዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደኋላ በማፈግፈግ ተጫውተዋል።
በጨዋታው 60ኛ ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ አህመድ ረሺድ ባጋጠመው ከባድ ጉዳት ምክኒያት በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን ጨዋታውም ለ10 ደቂቃዎች ያህል ተቋርጧል።
ጋቶች ፓኖም፣ ሳሙኤል ሳኑሚ እና ኤልያስ ማሞ ከርቀት ወደግብ አክርረው በመምታት ግብ ለማስቆጠር ቢሞክሩም ግብ ጠባቂው ኤሚክሪል ቢሊንጌን አልፎ በወልዲያ መረብ ላይ ያረፈ ኳስ ግን አልነበረም። አጥቂው አንዱአለም ንጉሴ በግንባሩ ገጭቶ ግብጠባቂው ሃሪሰን የያዘበት፣ እንዲሁም ሙሉጌታ ረጋሳ ከሳጥኑ ውጪ ወደግብ የመታው ኳስ በወልዲያ በኩል የተደረጉ ሙከራዎች ነበሩ።
ወልዲያዎች ጨዋታውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ በ9 ጨዋታዎች 10 ነጥብ በመሰብሰብ ደረጃቸውን ወደ 9ኛ ማሻሻል ችለዋል። ወልዲያ ከዚህም በተጨማሪ ክለቡ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የተጫወተበትን እና ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ ከተሸነፈ በኋላ ለ1 ዓመት ከ5 ወር ያህል ባለመሸነፍ ጉዞ የዘለቀበትን መልካቆሌ ስታዲየም በድል ተሰናብቷል። ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።