የኢትዮጵያ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ዛሬ ይጀመራል

በ16 የፕሪሚየርሊግ ክለቦች ብቻ እየተካሄደ ባለው የ2006 አም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ በሩብ ፍፃሜው ዛሬ 2 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ የአምናው ሻምፒዮን መከላከያ ከ ሐረር ቢራ ሲጫወት ፤ በሊጉ 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና ከ ሙገር ሲሚንቶ ይፋለማሉ፡፡

ወላይታ ድቻን በበዳሶ ሆራ ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፎ ወደ ሩብ ፍፃሜው የተቀላቀለው መከላከያ በ9፡00 መብራት ኃይልን በመለያ ምቶች ረትቶ ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀለው ሐረርቢራን ይገጥማል፡፡ መከላከያ ያለፈው አመት ሻምፒዮን ቢሆንም በፕሪሚየር ሊጉ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫው ያደረጓቸውን ያለፉት 9 ጨዋታዎች ካለ ድል ተጉዘዋል፡፡ ጦሩ ለመጨረሻ ጊዜ የነጥብ ጨዋታ ያደረገው ከ11 ቀን በፊት ከንግድ ባንክ ሲሆን በድራማዊት እይንቶች በታጀበው ጨዋታ 3-3 አቻ መውጣቱ ይታወሳል፡፡

ሐረር ቢራም እንደ መከላከያ ሁሉ በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ይገኛል፡፡ በሊጉ 13ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በርካታ የግብ እዳ የተሸከመ ክለብ ነው፡፡ የምስራቁ ክለብ ካለፉት 6 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ የተጫወተው ከ6 ቀናት በፊት በኢትዮጵያ ቡና 2-0 የተሸነፉበትን ጨዋታ ነው፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ዘንድሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም የ2ኛው ሳምንት ጨዋታ ላይ ተገናኝተው መካለከያ 2-1 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡


በ11፡30 ኢትዮጵያ ቡና ከ ሙገር ሲሚንቶ የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላው ዛሬ የሚካሄድ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ነው፡፡ ለአመታት ከሊጉ ይልቅ በጥሎ ማለፍ ውድድሮች ላይ የተሸለ ጉዞ የሚያደርገው ሙገር ሲሚንቶ ዛሬ የ5 ጊዜ ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ ቡናን ይፈትናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ያም ሆኖ በተከታታይ 7 የሊግ እና የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎችን በድል የተወጣው ኢትዮጵያ ቡና ወቅታዊ አቋም አስፈሪ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ዳሽን ቢራን 2-0 አሸንፎ ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀለ ሲሆን ሙገር በበኩሉ ሀዋሳ ከነማን 2-1 አሸንፎ የመጨረሻ ስምንት ቡድኖች ውስጥ ተቀላቅሏል፡፡

የሩብ ፍፃሜው ጨዋታ ነገም ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና አአ ስታድየም ላይ ይጫወታሉ፡፡ የደደቢት እና ንግድ ባንክ ላልታወቀ ጊዜ ተላልፏል፡፡

{jcomments on}

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *