የጨዋታ ሪፖርት | ወልድያ በአዲሱ ስታድየም የመጀመርያ 3 ነጥቡን አሳክቷል

በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድየም ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ወልድያ 2-1 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡ በአዲሱ ስታድየም የመጀመርያ ታሪካዊ ጎል እና 3 ነጥብ ማስመዝገብም ችሏል፡፡

በጨዋታው ሀዋሳ ከተማዎች በሌሎች የፕሪምየር ሊጉ ቡድኖች ላይ እንዳደረጉት ሁሉ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ቢሆንም ግልፅ የግብ እድል በመፍጠር ረገድ ግን አልተሳካላቸውም፡፡

በመጀመርያው ደቂቃ በማራኪ አጨዋወት ወደ ወልድያ የግብ ክልል ተጠግተው በግራ መስመር በኩል ወደ ሳጥኑ ያሻገሩትን አደገኛ ኳስ ቢሌንጌ ተቆጣጥሮታል፡፡ በ10ኛው ደቂቃ ደግሞ ከግብ ክልሉ መስመሩ ላይ የተገኘችውን ቅጣት ምት በድሩ መቶበሀዋሳዎች ተጨርፎ ወደ ውጭ ወጥቷል።

በ13 ደቂቃ ወልድያዎች ኳስ ሲመሰርቱ በፈጠሩት ስህተት ሀዋሳዎች የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ ቢያገኙም አልተጠቀሙበትም። በ15 ደቂቃ ያሬድ ሀሰን በአስገራሚ ብቃት ለበድሩ አመቻችቶ ቢያቀብለውም ኳሱ በመፍጠኑ የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ቀድሞ ይዞታል። ብዙም ሳይቆይ አቤጋ ጎል ቢያስቆጥርም በእቅስቃሴ ሒደት በእጁ በመግፋቱ ጎሉ ተሽሮ የቢጫ ካርድ ተመልክቷል፡፡

በ22ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ ያሻማውን ኳስ ጃኮ አረፋት ለፍሬው አመቻችቶ ቢያቀብለውም ፍሬው ኳሷን ወደ ውጭ ሰዷታል።

ከእረፍት መልስ 3 ግቦች ቢቆጠሩም ከመጀመሪያው አጋማሽ በባሰ የተቀዛቀዘ የጨዋታ እንቅስቃሴ ታይቷል።

በ58 ደቂቃ ያሬድ ሀሰን በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ ለአንዷለም ንጉሴ አመቻችቶለት “አቤጋ” ሲሞክር ሶሆሆ እና የግቡ ቋሚ ተጋግዘው ኳሱ በመውጣቱ የተገኘው የማዕዘን ምት ጋናዊው ተከላካይ አዳሙ መሀመድ ወደ ግብነት ቀይሮታል፡፡ አዳሙ በአዲሱ የሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድየም የመጀመሪያዋን ግብ በማስቆጠር ታሪካዊ ተጫዋች ለመሆንም በቅቷል፡፡

የወልድያ መሪነት የዘለቀው ለ6 ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ ከቅጣት ምት የተሞከረውን ኳስ ቢሌንጌ ሲመልሰው የሀዋሳ ተጫዋቾች አግኝተው በድጋሚ ሞክረው ቤሊንጌ በድጋሚ ቢመልሰውም በአቅራቢያው የነበረው ቶጓዊው አጥቂ ጃኮ አራፋት አግኝቶ ሀዋሳን አቻ አድርጓል፡፡ ጃኮ በ89ኛው ደቂቃ ሰአት ለማባከን ወድቋል በሚል በእለቱ ዳኛ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተመዞበት ከሜዳ ተወግዷል፡፡

ጨዋታው በተቃዘቀዘ ሁኔታ ዘልቆ በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ጫላ ድሪባ  በሳጥን ውስጥ ከሀዋሳ ተከላካዮች የቀማውን ኳስ ተጠቅሞ በጥሩ አጨራረስ ለወልድያ ጣፋጭ 3 ነጥብ ያስገኘበትን ጎል አስቆጥሯል፡፡

ድሉን ተከትሎ ወልድያ አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ተሸናፊው ሀዋሳ ከተማ በ7 ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ለመያዝ ተገዷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *