የጨዋታ ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል

በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ውሎ በአዲስ አበባ ስታድየም ብቸኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተገናኝተው ያለግብ አቻ ተለያይተዋል።

ከወልድያው ሽንፈት በኃላ ጥሩ እየተነቃቃ የነበረው እና ሳምንት ከጅማ ሶስት ነጥቦችን ይዞ የተመለሰው ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን በ ወላይታ ድቻ ላይ ካስመዘገበው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተገናኙበት የአዲስ አበባ ስታድየም የ10፡00 ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ የተጠበቀ ነበር።

ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞም የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ለቀድሞው የቡድናቸው ኮከብ ዳዊት እስጢፋኖስ በኢትዮጵያ ቡና መለያ የተነሳውን ፎቶግራፍ በስጦታነት ሲያበረክቱለት ለአሁኑ የቡድናቸው አምበል ጋቶች ፓኖምም  የሙሉ ቡድኑን ምስል የሚያሳይ ግዙፍ ፎቶግራፍ ሰጥተውታል ።

በአብዛኛው በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ላይ ባመዘነው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ፍልሚያ ኤሌክትሪኮች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ሲሆን ከተጋጣሚያቸው ግብ ክልል በጣም ርቀው ሲንቀሳቀሱ ለነበሩት ሁለቱ አጥቂዎቻቸው የመጨረሻ የግብ እድሎችን መፍጠር ግን ከብዷቸው ታይቷል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመጀመሪያው አጋማሽ ዳዊት እስጢፋኖስ በ8ተኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት መቶ ሀሪሰን ሄሱ ካወጣበት እና በ23ኛው ደቂቃ ፍፁም ገ/ማርያም ከሌላው አጥቂ ኢብራሂም ፍፋኖ ተቀብሎ ከሞከረው ለግብ የተጠጋ አጋጣሚ ሌላ የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ መስመር ያስጨነቀ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

እንደወትሮው የአማካይ መስመሩ የበላይነቱን ማሳየት ባልቻለበት የመጀመሪያ አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡና የጎል እድሎች ይፈጠሩ የነበሩት ከቆሙ ኳሶች እና መሀል ሜዳ ላይ ከሚነጠቁ ኳሶች መነሻነት ነበር። ያም ቢሆን ቡድኑ ከተጋጣሚው ይበልጥ የጎል እድሎችን መፍጠር ችሏል። በዚህም በአብዱልከሪም ሀሰን አማካይነት ከግራ መስመር የተነሱ ሁለት የቅጣት ምቶች ለቡድኑ ግልፅ የጎል ማግባት ዕድል የፈጠሩ ቢሆንም በጥሩ አቋቋም ላይ የነበሩት የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች በሚያስገርም ሁኔታ ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። በሰሞኑ የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ወሳኝ ግቦችን ሲያስቆጥር የሰነበተው አስቻለው ግርማም ከ እያሱ ታምሩ እንዲሁም ከያቡን ዊልያም በ8 እና 27ኛ ደቂቃዎች ላይ የተቀበላቸውን ኳሶች ቢሞክርም ወደግብ መለውጥ ግን አልተሳካለትም። ከአስቻለው ግርማ ሙከራዎች ሌላም የጋቶች ፓኖም የ33ኛ እና የ36ኛ የረጅም ርቀት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ።

ሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ በመሀል ተከላካይነት ጨዋታውን የጀመረውን አምበሉን አዲስ ነጋሽን ወደ ተከላካይ አማካይነት ሚና ያመጡት ኤሌክትሪኮች አለምነህ ግርማን በግራ መስመር ተከላካይነት ቀይረው በማስገባት ተስፋዬ መላኩን ከግራ መስመር ወደመሀል ተከላካይነት አምጥተውታል። የቀኝ መስመር አማካይ ክፍል ላይም በወላይታ ድቻው ጨዋታ ጥሩ የተንቀሳቀሰውን በሀይሉ ተሻገርን በዋለልኝ ገብሬ ቀይረዋል። ይህ የአማካይ እና የተከላካይ መስመር ሽግሽግ ግን እንደታሰበው መልካም ውጤት አላመጣም። ቡድኑ መሀል ሜዳ ላይ የነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ የበላይነትም በተጋጣሚው ተወስዶበት ታይቷል።

በቡናማዎቹ በኩል ሰሞኑን ተደጋጋሚ የመሰለፍ እድል እያገኘ የነበረው አብዱልከሪም ሀሰን በጨዋታው ላይ ጥሩ አለመንቀሳቀሱን ተከትሎ በ59ኛው ደቂቃ ላይ በኤልያስ ማሞ ከተተካ በኃላም የወትሮውን የኢትዮጵያ ቡናን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መመልከት ችለናል። ይህንን ተከትሎም ቡናዎች ይበልጥ ወደጨዋታው እየገቡ እና ተደጋጋሚ ጫናም እየፈጠሩ ወደጎል መቃረብ ችለው ነበር።  ነገር ግን ይህን ጫና ወደ ግልፅ ግብ የማስቆጠር አጋጣሚ ከመቀየራቸው በፊት ኤሌክትሪኮች ከሁለቱ የፊት አጥቂዎች መካከል ኢብራሂም ፍፋኖን ወደ ቀኝ መስመር አማካይነት ቦታ በመውሰድ እና የአማካይ መስመር ላይ ቁጥር በመጨመር የተወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ማስመለስ ችለዋል።

በዚህ የኤሌክትሪኮች ወሳኝ ቅያሪ ምክንያትም ቀድሞ በተጋጣሚው ሜዳ ላይ ብዙ ኳሶችን የመቀባበል እድል አግኝቶ የነበረው ኢትዮጵያ ቡናም ከመልሶ ማጥቃት የሚነሱ ኳሶችን ለመጠቀም የተገደደ ይመስል ነበር። በ83ተኛው ደቂቃ ላይም አስቻለው ግርማ ከኤልያስ ማሞ የተቀበለው እና ለጥቂት ያመከነው ኳስ የዚህ እንቅስቃሴ ውጤት ነበር።

ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው በብሩክ አየለ እና በበሀይሉ ተሻገር ከርቀት የሞከሯቸው የ56ተኛ እና የ71ኛ ደቂቃ ሙከራዎች ይጠቀሱ እንደሆን እንጂ ብልጫ በወሰዱባቸው አጋጣሚዎች ይዘዋቸው የሚገቡ ኳሶች በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ በተለይም በቡድኑ ዋና ፈጣሪ ተጨዋች ዳዊት እስጢፋኖስ ደካማ እንቅስቃሴ ምክንያት በተደጋጋሚ ሲበላሹ ተስተውሏል። በቡድኑ አማካይ መስመር ላይ በተለይም አምበሉ አዲስ ነጋሽ በጉዳት ተቀይሮ ከወጣ በኃላ የቦታ ለውጥ ያረገው ብሩክ አየለ የተጋጣሚውን የመሀል ሜዳ ጫና በመቋቋም ያሳየው ድንቅ እንቅስቃሴም ከተመልካች ሙገሳን ያስቸረው ነበር። ያም ሆኖ ኤሌክትሪኮችም እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ለመጨረሻ አጥቂዎቻቸው በቂ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ እና ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል።

በውጤቱም መሰረት አንድ አንድ ነጥብ የተጋሩት ሁለቱ ተጋጣሚዎች በሊጉ በነበሩበት ማለትም ኢትዮጵያ ቡና በ8ኛ እንዲሁም ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ12ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጡ ሆኗል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *