በ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ኢትዮጵያ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱም ክለቦች አሰልጣኞች ስለጨዋታው ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ብርሃኑ ባዩ – አትዮ ኤሌክትሪክ
ስለጨዋታው
“ከዛሬው ጋር ስምንተኛ ጨዋታ ነው አቻ ስንወጣ፡፡ በተለይ ከዚህ በፊት የነበሩ ጨዋታዎች በርካታ የግብ እድሎች እየፈጠርን ነበር አቻ የወጣነው፡፡ ዛሬ ግን ጨዋታው ተመጣጣኝ ነበር ፤ ሁለታችንም ኳስ ነበር የምንጫወተው፡፡ ብዙም ለግብ የቀረቡ እድሎች ሁለታችንም አላገኘንም፡፡ ቡናዎች ወደመጨረሻ አከባቢ ያገኟት ኳስ በጣም አደገኛ ነበረች፡፡ ዞሮ ዞሮ ጥሩ እና ተመጣጣኝ ጨዋታ ነበር፡፡”
“ወደ መጨረሻው አከባቢ ሁለቱም ቡድኖች ተዳክመዋል፡፡ እንዳያችሁት ወደ ግብ እየቀረበ የነበረው ቡና ሳይሆን ኤሌክትሪክ ነው፡፡ ነገር ግን በርካታ ኳሶችን ከድካም በኃላ ያገኙ ስለነበር ወደ ውጤት አልተቀየረም፡፡”
የአጨራረስ ድክመት
“ሲጀመር ጀምሮ የነበረው ችግር ይህ ነው፡፡ ከኃላ ደግሞ በቀላሉ ግብ ይቆጠሩብን ነበር፡፡ ብዙ ኳሶች እንስታለን ፤ ግን ቀላል ኳሶች ይገቡብናል፡፡ ሁለቱ ቦታዎች ላይ ችግር አለብን፡፡ ዛሬም የተየው ነገር ይህ ነው፡፡ ወደ መጀመሪያው አከባቢ አይታችሁ እንደሆነ ፍፁም የሳታት ኳስ መረጋጋት ቢችል ኖሮ የጨዋታው መልክ ሌላ ይሆን ነበር ፤ ግን አልሆነም፡፡ ይህ የቆየ ችግር ነው ፤ በሂደት በራስ መተማመኑ እየመጣ ሲሄድ ያሉት ልጆች ግብ ማግባት ይጀምራሉ ብዬ አስባለው፡፡”
የተጫዋቾች ቅያሪ
“ለውጡን ያያችሁት ይመስለኛል፡፡ (አሸናፊ ሽብሩ እና ዋለልኝ ገብሬ) ኳሶች እነሱ ጋር በተደጋጋሚ ይበላሹ ነበር፡፡ ኳሶች በፍጥነትም ወደፊት አይሄዱም ነበር፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ነበር ሁለት ተጫዋቾችን በአንድ ጊዜ የቀየርኩት፡፡”
ገዛኸኝ ከተማ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለጨዋታው
“የዛሬው ጨዋታ ጥሩ ነው፡፡ ሁለታችንም ጥሩ ተጫውተናል፡፡ እንዳያችሁት እንግዲህ ውጤቱ በእንደዚህ ዓይነት መልኩ ተጠናቅቋል፡፡ በእርግጥ ውጤቱ ያደረግነውን እንቅስቃሴ አይገልፀውም፡፡ ግን እግርኳስ ነው የመጣውን ነገር መቀበል አለብን፡፡ ውጤቱን በፀጋ ተቀብለናል ምንም ማድረግ አንችልም፡፡”
በጫና ውስጥ መጫወት
“እንደዚህ ዓይነት ጨዋታዎች ሁልግዜም ጫና ውስጥ ይከቱሃል፡፡ ምክንያቱም ወደ ውጤት እየሄድን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ነገር ጫና ውስጥ የጣላቸው ልጆች ነበሩ፡፡ ከዛ በኃላ ማስተካከያ አድረገን የተሻለ ነገር ማሳየት ችለናል፡፡”