የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት 7 ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ተካሂደው አዳማ በጊዜያዊነት ወደ ሊጉ አናት የወጣበትን ፣ ደደቢት የውድድር ዘመኑ የመጀመርያ የክልል ሜዳ ድሉን ፣ ሲዳማ ቡና ወደ መሪዎቹ የተጠጋበትን ፣ አአ ከተማ ከ8 ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት በኋላ ወደ ድል የተመለሰበትን እንዲሁም ወልድያ የአዲሱ ስታድየም የመጀመርያ ድሉን አስመዝግቧል፡፡
አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው አዳማ ከተማ 2-1 በማሸነፍ የሊጉም መሪነት ነገ ጨዋታ ከሚያደርገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተረክቧል፡፡ ድንቁ ወጣት አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው በ8ኛው ደቂቃ ሁለት ተጫዋቾችን በማለፍ አዳማን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ቢያስቆጥርም ከ1 ደቂቃ በኋላ አንድነት አዳነ ከወንድሜነህ ዘሪሁን የተሻገረውን የቅጣት ምት ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር አርባምንጭን አቻ አድርጓል፡፡ ከ8 ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሱራፌል በድጋሚ ግብ አስቆጥሮ አዳማን ቀዳሚ ሲያደርግ በ24 ነጥብ ሊጉን እንዲመራ ያስቻለውን 3 ነጥብ እንዲያገኝም አስችሏል፡፡
ወደ ሶዶ ያቀናው አዲስ አበባ ከተማ ወላይታ ድቻ ላይ ያልተጠበቀ ድል በማስመዝገብ የሰንጠረዡን ግርጌ ለሀዋሳ ከተማ አስረክቧል፡፡ ኃይሌ እሸቱ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ የመዲናዋን ክለብ ብቸኛ የድል ግብ አስቆጥሯል፡፡ ድሉ አዲስ አበባ ከተማ ከ8 ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድል የተመለሰበት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ይርጋለም ሲዳማ ቡና ስታድየም ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና 1-0 በማሸነፍ የመሪዎቹን ፉክክር ተቀላቅሏል፡፡ ናይጄርያዊው አጥቂ ላኪ በሪለዱም ሳኒ የሲዳማን ብቸኛ የድል ግብ አስቆጥሯል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በይርጋለም ባደረጓቸው ያለፉት 6 ተከታታይ ጨዋታዎች ከተመዘገቡት የአቻ ውጤቶች በኋላ የመጀመርያ ድል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
የድሬዳዋ ስታድየም እድሳት ላይ በመሆኑ ምክንያት የሜዳው ጨዋታውን በሐረር አሚር አብዱላሂ ስታድየም ያደረገው ድሬዳዋ ከተማ ከ መከላከያ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ቴዎድሮስ ታፈሰ በ80ኛው ደቂቃ በቅጣት ምት ግሩም ግብ አስቆጥሮ ጦሩን ቀዳሚ ቢያደርግም ሌላው ተቀይሮ የገባው በረከት ይስሃቅ ከረጅም ርቀት የተላከውን የቅጣት ምት በግንባሩ በመግጨት ድሬዳዋን አቻ አድርጓል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች ወልድያ እና ደደቢት ተጋጣሚዎቻቸውን ሲያሸንፉ ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡ የሶስቱን ጨዋታዎች የጨዋታ ሪፖርት ከዚህ በታች ያገኛሉ፡-
ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና 0-0 ኢትዮ ኤሌክትሪክ