የጨዋታ ሪፖርት ፡ አሰልጣኝ ደረጄ በላይ “የመጨረሻ” ባሉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን ነጥብ አስጥለዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ተካሂዶ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ቡና ሳይሸናነፉ 1-1 ተለያይተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳግም መሪነቱን ከአዳማ ከተማ የመውሰድ እድልን ሲያመክን በደካማ የሊግ ጉዞ ላይ የተገኘው ጅማ አባ ቡና ወሳኝ ነጥብን ከሜዳው ውጪ ማግኘት ችሏል፡፡

የባለሜዳዎቹ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ከወትሮው በተለየ ፈረሰኞቹ ወደ ግብ ለመሞከር ሲቸገሩ ነበር፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ጥብቅ መከላከልን እና ፈጣን የሆነ የመልሶ ማጥቃትን የመረጡት አባ ቡናዎች በተደጋጋሚ የቅዱስ ጊዮርጊስን የኃላ መስመር ሲፈትሹ ነበር፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በ9ኛው ደቂቃ አሜ መሃመድ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን መልሶበታል፡፡ ከደቂቃ በኃላ አባ ቡናዎች መሪ መሆን የሚችሉበትን እድል በቴዎድሮስ ገ/ፃዲቅ ነኩል ሞክረው ኳሷ ዓላማዋን ሳትጠብቅ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡ አሁንም በ13ኛው ደቂቃ ከመሃል ወደ ሳጠኑ የተሻገረለትን ኳስ በአግባቡ የተቆጣጠረው አሜ ግብ ጠባቂው ፍሬውን ቢያልፈውም ሙከራው ግን በማይታመን መልኩ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ የፈረሰኞቹ የኳስ ቁጥጥር በጅማ አባ ቡና ሜዳ ላይ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል የግብ ማግባት ሙከራ ግን ማድረግ አልቻሉም ነበር፡፡

በ31ኛው ደቂቃ አሜ ሱራፌል አወል የጨረፈለትን ኳስ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ሲቀር ከአምስት ደቂቃዎች በኃላ ጅማ አባ ቡናዎች ግብ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ኪዳኔ አሰፋ በግምት ከ18 ሜትር ርቀት ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብነት ቀይሮታል፡፡ ግብ ጠባቂው ፍሬው ኳሷን ለማውጣት ያልተሳካ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡

ከግቡ መቆጠር በኃላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ቅብብል በራሳቸው የሜዳ ክልል ብቻ ተወስኖ ቆይቷል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሲጠናቀቅም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በክለባቸው ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ላይ ተቀውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ በተለይ በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በካታንጋ የነበሩ የክለቡ ደጋፊዎች ‘የክቡር ይደነቃቸውን ዘመን እናፍቃለን’ እና በእንጅሊዘኛ ‘Mart Nooj Out’ የሚል ባነር አሳይተዋል፡፡ የሆላንዳዊውን አሰልጣኝ ስም እየጠሩም ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው 45 በተሻለ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል፡፡ በ54ኛው ደቂቃ ናትናኤል ዘለቀ ከርቀት አክርሮ የሞከረው ኳስ የአባ ቡናው ግብ ጠባቂ ሙላት አለማየሁ ወደ ውጪ አውጥቶበታል፡፡ ጅማ አባ ቡናዎች በተደጋጋሚ የተጋጣሚያቸው ያልተሳካ የኳስ ቅብብልን እየተጠቀሙ በመልሶ ማጥቃት ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል፡፡ በ69ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ የአባ ቡና ተከላካዮች በአግባቡ ማውጣት ተስኗቸው በቅርብ ርቀት የነበረው ሳላዲን ሰዒድ ኳሷን ወደ ግብነት ቋይሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን አቻ አድርጓል፡፡

ከደቂቃዎች በኃላ በሁለተኛው አጋማሽ አዳነ ግርማ ወደግብ ያላከው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፋ ግብ ሳትሆን ቀርታለች፡፡ በ75ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጣሪው ኪዳኔ ከአሜ ጥሩ ኳስ ቢቀብልም አገባ ተብሎ ሲጠበቅ ኳሷን ወደ ውጪ ሰዷታል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ሱራፌል አወል በቅጣት ምት የሞከረው ሙከራ በግቡ አናት ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ በ80ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ከግራ መስመር ኳስን ወደ አደጋ ክልሉ ያላከው ኳስ የአባ ቡና ተከላካዮች ሲጨርፉ በቅርብ ርቀት የነበረው ሳላዲን በማየታመን መልኩ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ አባ ቡናዎች  የተከላካይ ክፍል ክፍተት ታይቶበታል፡፡ በጭማሪው ደቂቃ ላይ አዳነ በሳጥኑ ውስጥ ሆኖ የሞከረው ሙከራ ሙላት በቀላሉ ይዞበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ 1 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን ከጅማ አባ ቡና ጋር መለያየታቸው እውን እየሆነ የመጣው አሰልጣኝ ደረጄ በላይ በቀኝ ከማን አንሼ ለተገኙት የጅማ አባ ቡና ደጋፊዎች ስንብት የሚመስል ሰላምታ ሲያቀርቡ ተስተውሏል፡፡

በደረጃ ሰንጠረዡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሪው አዳማ ከተማ በሁለት ነጥቦች ተበልጦ በ22 ነጥብ ሶስተኛ ሲሆን ጅማ አባ ቡና በ10 ነጥብ 14ኛው ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *