ዝውውር | ሀዋሳ ከተማ ኮትዲቯራዊ ተከላካይ አስፈረመ

ሀዋሳ ከተማ ኮትዲቯራዊው ተከላካይ መሀመድ ሲይላን ከሱዳኑ አል-አህሊ ሼንዲ አስፈርሟል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘውና በሊጉ ከፍተኛውን የግብ መጠን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ የተከላካይ መስመሩን ችግር ለመቅረፍ ልምድ ያለው መሃመድን ዝውውር እንዳጠናቀቁ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሱዳኑ አል አህሊ ሸንዲ ቆይታቸው ከመሀመድ ሲይላ ጋር አብረው የሰሩ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ ዳግም ይገናኛሉ፡፡ የ26 አመቱ ተጫዋች በሱዳኑ ክለብ የነበረው ኮንትራት በአመቱ መጀመርያ በመጠናቀቁ ሀዋሳን በነፃ ዝውውር ሲቀላቀል የ1 አመት ከ6 ወራት ኮንትራት ተፈራርሟል፡፡ ተጫዋቹ በ2ኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለክለቡ ተሰልፎ መጫወትም ይጀምራል፡፡ 

መሀመድ በአልአህሊ ሸንዲ የተሳካ ጊዜያትን ያሳለፈ ሲሆን ከክለቡ ወሳኝ ተጫዋቾችም አንዱ ነበር፡፡ ለኮትዲቯር ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው ሲይላ ከአህሊ ሸንዲ በፊት በቱኒዚያው ቤዘርቴይን ፣ በቡርኪና ፋሶው አርሲ ቦቦ እና በሀገሩ ክለብ አፍሪካ ስፖርትስ ተጫውቷል፡፡ በሱዳኑ ታላቅ ክለብ ኤልሜሪክ ኦምዱርማንም የ6 ወራት የውሰት ቆይታ ነበረው፡፡

ሀዋሳ ከተማ የተከላካይ መስመሩን ለማጠናከር በስፋት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የተለያየው አይዛክ ኢሴንዴን ወደ ክለቡ ለማምጣት በድርድር ላይ መሆናቸውን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ከዩጋንዳ የአፍሪካ ዋንጫ ቡድን ጋር ጋቦን የሚገኘው አይዛክ ዩጋንዳ በጊዜ ከአፍሪካ ዋንጫው መሰናበቷን በማረጋገጧ ምናልባትም በቀጣዩ ሳምንት ለሀዋሳ ከተማ ሊፈርም ይችላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *