ሱዳናዊው የቀድሞ አል አህሊ ሸንዲ እና ኤል ሜሪክ ኦምዱርማን የመሃል ተከላካይ መሐመድ አሊ ኤል ኪደር (በቅፅል ስሙ – መሐመድ ሳፋሪ) ለሀዋሳ ከተማ እንደፈረመ ክለቡ አስታውቋል።
ኤል ኪደር ለሀዋሳ የፈረመው በ6 ወራት የውሰት ውል ሲሆን ወርሀዊ 3750 ዶላር ደሞዝ እንደሚከፈለው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በሱዳን ፕሪምየር ሊግ እ.ኤ.አ. ከ2004 ጀምሮ ለ13 ተከታታይ አመታት መጫወት የቻለው ሳፋሪ በሃገሩ እና በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ላይ በመሳተፍ ሰፊ ልምድ ያካበተ መሆኑ ደካማ ለሆነው የሀዋሳ ከተማ የተከላካይ መስመር ጥንካሬ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። የ32 ዓመቱ ተከላካይ በሱዳኑ ታላቅ ክለብ ኤል ሜሪክ ኦምዱርማን በሚጫወትበት ወቅትም ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን በመጠራት በ19 ጨዋታዎች መሰለፍ ችሏል።
በፕሪምየር ሊጉ በ12 ጨዋታዎች 19 ግቦችን አስተናግዶ በ8 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት ተጫዋቾችን በማስፈረም በሁለተኛው ዙር ተጠናክሮ ለመቅረብ ጥረት እያደረገ ይገኛል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተም በሱዳኑ አህሊ ሸንዲ በነበራቸው ቆይታ አብረዋቸው የሰሩ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ እያመጡ ሲሆን ከመሐመድ ሳፋሪ በተጨማሪ ኮትዲቯራዊው የቀድሞ የሸንዲ ተከላካይ መሐመድ ሲይላ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሀዋሳ ማምራቱን መዘገባችን ይታወሳል።
የተከላካይ መስመሩን ለማጠናከር በስፋት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ከሁለቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የተለያየውን ኡጋንዳዊ ተከላካይ አይዛክ ኢሴንዴ ወደ ክለቡ ለማምጣት በድርድር ላይ ነው።
© በድረገፁ የሚወጡ ፅሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሰ በቀር ሙሉ ለሙሉ የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ ፅሁፎቹን በሌላ ሚድያ ሲጠቀሙ ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡