የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ [የኢትዮጵያ ዋንጫ] የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች የካቲት 11 እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
ውድድሩ ከ16 የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በተጨማሪ 5 የከፍተኛ ሊግ ክለቦች የተካተቱበት መሆኑ ካለፉት አመታት የተለየ ያደርገዋል፡፡ ከሚሌንየሙ መጀመርያ በኋላ ከፕሪምየር ሊግ ክለቦች ውጪ ያሉ ክለቦች ሲሳተፉም የመጀመርያ ይሆናል፡፡
ፌዴሬሽኑ በውድድር አመቱ መጀመርያ የከፍተኛ ሊግ ክለቦች በጥሎማለፉ እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን እንደሚወዳደሩ የተገለፁት ግን 5 ብቻ ናቸው፡፡
የጥሎ ማለፉ የዕጣ ማውጣት ስነስርአት እና በውድድሩ አካሄድ ላይ የሚደረገው ውይይት ከፕሪምየር ሊጉ 1ኛ ዙር ግምገማ ጋር በጋራ የካቲት 7 ሶዶ ከተማ ላይ ይደረጋል፡፡ በውድድሩ የሚሳተፉ የከፍተኛ ሊግ ክለቦችም በእለቱ ይፋ ይደረጋሉ ተብሏል፡፡
የ2009 የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ አሸናፊው ክለብ በ2018 ቶታል ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ የመሳተፍ እድል ሲያገኝ የአምናውን ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊስ በማሸነፉ ለፍጻሜ የደረሰው መከላከያ በ2017 የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመካፈል እድል አግኝቷል፡፡
© በድረገፁ የሚወጡ ፅሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሰ በቀር ሙሉ ለሙሉ የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ ፅሁፎቹን በሌላ ሚድያ ሲጠቀሙ ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡