የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 10ኛ ሳምንት ዛሬ አበበ ቢቂላ ላይ በተደረጉ 2 የምድብ ሀ ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡ ኢትዮጵያ መድን ድል ሲያስመዘግብ ውሃ ስፖርት እና ሱሉልታ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
08:00 ላይ ቡራዩ ከተማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ መድን ከእረፍት በፊት እና በኃላ በተቆጠሩ ሁለት ሁለት ግቦች 4-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡
ጀማል አህመድ ገና በ5ኛው ደቂቃ መድንን ቀዳሚ ሲያደርግ አብይ ቡልቲ በ28ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን አክሎ በመድን 2-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና እና አአ ከተማ አማካይ ሐብታሙ ረጋሳ እና ተቀይሮ የገባው አስራት ሸገሬ ተጨማሪ ግቦች አክለው ጨዋታው በሰማያዊዎቹ 4-0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ መድን በ15 ነጥብ ደረጃውን ወደ 4 ከፍ ሲያደርግ ቡራዩ ከተማ በ13 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
10:00 ላይ በኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት እና ሱሉልታ ከተማ መካከል የተካሄደው ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ሱሉልታ ሁለት ጊዜ የመምራት እድል ባገኘበት ጨዋታ መጨረሻ ከፍተኛ ውዝግብ ተከስቷል፡፡
ሱሉልታ ከተማ በአምበሉ አቤል ታሪኩ የቅጣት ምት ግብ ለረጅም ደቂቃዎች መሪ መሆን ችሎ ነበር፡፡ ሳሙኤል ወንድሙ ባለ ሜዳዎቹን አቻ ማድረግ ቢችልም ሱሉልታዎች በይድነቃቸው የሺጥላ ግብ በድጋሚ መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ የሽርፍራፊ ደቂቃዎች እድሜ ሲቀረው ደሳለኝ ወርቁ ለውሃ ስፖርት ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
በጨዋታው መሃል በተደጋጋሚ ሲታይ የነበረው ጉሽሚያ እና ሽኩቻ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም አይሎ የሁለቱ ቡድን አባላት ጸብ ውስጥ የገቡ ሲሆን የመጫወቻው ሜዳ በተመልካቾች እና የጸጥታ ሃይሎች ተወሮ ተስተውሏል፡፡ እንዲህ አይነት ወሰን ያጡ ጠቦች በሊጎቻችን እየተለመዱ መምጣታቸው አሳሳቢ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡
የከፍተኛ ሊጉ ነገ ሲቀጥል በመላ ሃገሪቱ 14 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም እንደተለመደው ጨዋታዎች በቀጥታ የውጤት መግለጫ ወደ እናንተ ታደርሳለች፡፡
ምድብ ሀ
ቅዳሜ ጥር 20 ቀን 2009 | |||
FT | ኢት መድን | 4-0 | ቡራዩ ከተማ |
FT | ኢት ውሃ ስፖርት | 2-2 | ሱሉልታ ከተማ |
እሁድ ጥር 21 ቀን 2009 |
|||
ባህርዳር ከተማ | 08:00 | ወልዋሎ አ.ዩ. | |
ለገጣፎ ለገዳዲ | 09:00 | ሽረ እንዳስላሴ | |
አክሱም ከተማ | 09:00 | አአ ፖሊስ | |
ሰ.ሸ.ደ. ብርሃን | 09:00 | ሰበታ ከተማ | |
ወሎ ኮምቦልቻ | 09:00 | መቐለ ከተማ | |
አማራ ውሃ ስራ | 10:00 | አራዳ ክ.ከ |
ምድብ ለ
እሁድ ጥር 21 ቀን 2009 |
||
ደቡብ ፖሊስ | 09:00 | ድሬዳዋ ፖሊስ |
ጅማ ከተማ | 09:00 | ካፋ ቡና |
ጂንካ ከተማ | 09:00 | ፌዴራል ፖሊስ |
አርሲ ነገሌ | 09:00 | ስልጤ ወራቤ |
ወልቂጤ ከተማ | 09:00 | ሻሸመኔ ከተማ |
ዲላ ከተማ | 09:00 | ሀዲያ ሆሳዕና |
ነገሌ ቦረና | 09:00 | ሀላባ ከተማ |
ናሽናል ሴሜንት | 10:00 | ነቀምት ከተማ |