የ2017 ቶታል የአፍሪካ ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ቅዳሜ ምሽት ሲጀምሩ ካሜሮን እና ቡርኪናፋሶ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያመሩበትን ድል አስመዝግበዋል፡፡ ቡርኪናፋሶ በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ቱኒዚያን ስታሸንፍ ካሜሮን በመለያ ምት ሴኔጋልን ከውድድር አስመጥታለች፡፡ ውድድሩ በተመልካች ድርቅ መመታቱን ቀጥሏል፡፡
ቡርኪናፋሶ ቱኒዚያን 2-0 በመርታት ወደ ግማሽ ፍፃሜው አልፋለች፡፡ ሊበርቪል ላይ በተደረገው ጨዋታ ፈረሰኞቹ በመጀመሪያው አጋማሽ በፕሪጁስ ናኮልማ እና በርትራንድ ትራኦሬ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በመጀመሪያ አጋመሽ ሲያደርጉ የካርቴጅ ንስሮቹ በጠሃ ያሲን ከኔሲ አማካኝነት ወደ ግብ ሞክረዋል፡፡ በ80ኛው ደቂቃ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አንጋፋው አጥቂ አሪስቲድ ባንሴ በቅጣት ምት ሃገሩን መሪ አድርጓል፡፡ ከአራት ደቂቃዎች በኃላ ቱኒዚያዎች የአቻነት ግብ ለማግኘት ሙሉ ለሙሉ በማጥቃት ወረዳው ላይ መገኘታቸውን ተከትሎ ፈረሰኞቹ በመልሶ ማጥቃት ሁለተኛ ግባቸውን በፕሪጁድ ናኮልማ አማካኝነት ከመረብ አዋህደዋል፡፡ የቱኒዚያው ግብ ጠባቂ አይመን ማትሉቲ ከግብ ክልሉ ርቆ ወጥቶ ናኮልማን ለማቆም ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም፡፡ ቡርኪናፋሶ ከዚህ ቀደም ሁለት ግዜ ብቻ በአፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ መሳተፍ የቻለች ሲሆን የአሁኑን ጨምሮ ተጫወተችባቸው የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ተሸንፋ አታውቅም፡፡ ቱኒዚያ በ2015 ከሩብ ፍፃሜ የተሰናበተች ሲሆን አሁንም ዳግም ከሩብ ፍፃሜው ወጥታለች፡፡ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በካፍ የተመረጠው ናኮልማ ነው፡፡
እምብዛም የማለፍ ግምት ያልተሰጣት ካሜሮን ዋንጫውን ያነሳሉ ተብላ የተጠበቀችውን ሴኔጋልንን በመለያ ምት 5-4 በማሸነፍ ጣፍጭ ድል ተቀዳጅታለች፡፡ ፍራንስቪል ላይ በተደረገው ፍልሚያል የቴራንጋ አንበሶቹ በጨዋታው ላይ በሙከራ ረገድ የተሻሉ ነበሩ፡፡ ማሜ ቤራም ዲዩፍ እና ቼክ ኮያቴ በመጀመሪያ አጋማሽ ለግብ የቀረቡ መከራዎች ማድረግ ችለዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የማይበገሩት አንበሶቹ የሴኔጋልንን የኃላ መስመር መፈተሽ የቻሉበትን ሙከራዎች ሮበርት ታምቤ እና ቤንጃሚን ሙካንጆ አድርገዋል፡፡ ጨዋታው በመደበኛው ክፍለ ግዜ ያለግብ አቻ በመጠናቀቁ ቡድኖቹ ወደ ጭማሪ ሰዓት ያመሩ ሲሆን የሴኔጋሉ ግብ ጠባቂ አቡዱላሂ ዲያሎ የጃክዌስ ዞን ሙከራ በማምከን ቡድኖቹ ወደ መለያ ምት ማምራት ችለዋል፡፡ የሴኔጋሉ ሰይዶ ማኔን ምት ፋብርሶ ኦንዶ ሲያምክንበት ቪንሶ አቡበከር ወሳኟን ምት በማስቆጠር ካሜሮንን አሸናፊ አድርጓል፡፡ በ2002 የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ በተመሳሳይ ካሜሮን ሴኔጋልን በመለያ ምት ማሸነፏ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የአሁኑ የሴኔጋል አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ መለያ ምታቸውን ካመከኑ ተጫዋቾች መካከል ነበር፡፡ ሲሴ ሃገሩ ሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫ የምታነሳ ከሆነ ድሬድ ፀጉሩን እንደሚቆረጥ መናገሩ ይታወሳል፡፡ የካሜሮኑ ኦንዶ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡
ጨዋታዎቹ ዛሬም ሲቀጥሉ ጋና ከዲ.ሪ. ኮንጎ ምሽት 1፡00 እንዲሁም ግብፅ ከሞሮኮ ምሽት 4፡00 በኦይም እና ፖር ዠንቲል ይጫወታሉ፡፡ የኮንጎ እና ጋና አሸናፊ ካሜሮንን እንዲሁም የሞሮኮ እና ግብፅ አሸናፊ ቡርኪናፋሶን በግማሽ ፍፃሜው የሚያገኝ ይሆናል፡፡
የፎቶ ምንጭ፡ AFP