የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተደርጎ ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 5-2 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱም ክለቦች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ
ስለጨዋታው እና የመከላከል ድክመት
“ከመጀመሪያም አቅደን የተነሳነው ሙሉ በሙሉ በማጥቃት የተሻለ ነገር ይዘን ለመውጣት ነው፡፡ በዚህ መሃል ያሉ ሽግግሮች ትንሽ ችግር ውስጥ ከተውናል፡፡ እነዛን በቀጣይ እናሰተካክላለን ብለን እናስባለን፡፡”
“ኳስን መስርቶ መጫወት ላይ አይደለም ችግር ያለብን ፤ አንዳንድ ጊዜ ከመዘናጋት የሚፈጥሯት ስህተት ነው፡፡ በቀጣይ አርመን የተሻለ ነገር ለመስራት እንሞክራለን፡፡”
የቡድኑ ውጤት ስለመሻሻል
“ቡድኑ የሚታወቅበትን ጨዋታ ማምጣት ነበረብን፡፡ ከዚህ በፊት ቡድኑ የሚታወቅበትን ጨዋታ አጥቶት ነበር፡፡ ረጅም ኳስ ነበር እንዲጫወቱ የሚፈቀደው፡፡ ይህንን በማስቀረት ወደ ራሳችን ጨዋታ ተመልሰን የተሻለ ነገር ለመስራት እየሞከርን ነው፡፡”
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም
ስለጨዋታው
“የዛሬው ጨዋታ ውጤቱ ገላጭ ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ቡና ከእኛ በሁሉም ነገር የተሻለ ስለነበር አሸንፎ ሊወጣ ችሏል፡፡ በእኛ በኩል ደግሞ እንደምታውቁት የስኳድ መመናመን ይታያል፡፡ በዛሬው ጨዋታ እንኳን ሶስቱ አማካዮቻችን አዲሱ፣ ታዲዮስ እና ፍቅረየሱስ በጉዳት ወጥተዋል፡፡ ጂብሪል እና በረኛችን ፊቮ በጉዳት አልተሰለፉም፡፡ በተቻለ መጠን ጥሩ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ከእኛ የተሻለው ቡና ስለነበር አሸንፎናል፡፡ ውጤቱን በፀጋ ተቀብለናል፡፡ ከዚህ በኃላ ባሉን ጨዋታዎች አቅማችን የፈቀደውን አድርገን የምንሰራውን ስራ ሰርተን ጠንካራ ቡድን ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን፡፡”
“የልምድ አጨዋወት ችግር ነበር፡፡ ቡድናችን ኳስ እግሩ ላይ ሲገባ ካልሆነ በስተቀር ኳሱን ሲያጣ ምንም የሚሰራው ስራ አልነበረም፡፡ ለተጋጣሚያችን ነፃነት ሰጥተን ነበር ስንጫወት የነበረው፡፡ እንደፈለጉ ኳስ እንዲገፉ ይፈቅዱላቸዋል፡፡ ኳስ እንሲያቀብሉ እና ነፃ ቦታ ይፈቅዱላቸዋል፡፡ ኳስ እንዲያዘጋጁም ይፈቅዱላቸው ነበር፡፡ ይህንን ደግሞ ለኢትዮጵያ ቡና ፈቀድክ ማለት በነፃነት ይጫወታሉ ማለት ነው፡፡ ዛሬ ከፍተን መጫወታችን ነው እንጂ የተለየ ታክቲክ ይዘን ብንገባ ኖሮ እነዚህ ግቦች ላይቆጠሩ ይችሉ ነበር፡፡”