“የተሰጠኝ የጨዋታ ነፃነት ጥሩ አቋም እንዳሳይ ረድቶኛል” ወንድሜነህ ዘሪሁን

ወንድሜነህ ዘሪሁን በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት አርባምንጭ ከተማን ከተቀላቀለ በኋላ ምርጥ አቋም በወጥነት እያሳየ ይገኛል፡፡ የአጥቂ አማካዩ 4 ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ሲያቀብል 3 ጎል በስሙ አስመዝግቧል፡፡ በአርባምንጭ ደጋፊዎች የሚዘጋጀውን የወሩ ኮከብ ተጫዋች ምርጫ ለተከታታይ ሁለት ወራት ሲያሸንፍ በሶከር ኢትየዮጵያ የታህሳስ ወር ምርጥ ቡድን ውስጥም ተካቷል፡፡

ወንድሜነህ በወቅታዊ አቋሙ እና አጠቃላይ የእግርኳስ ህይወቱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን አጠር ያለ ቆይታ እነሆ ብለናል፡፡


በበርካታ ክለቦች (ሙገር ፣ መከላከያ ፣ ሀዋሳ ፣ ኤሌክትሪክ ፣ አዳማ እና አርባምንጭ) ተጫውተሃል፡፡ የእግር ኳስ ህይወትህን እንዴት ትገልጸዋለህ?

ከዚህ ቀደም የበርካታ ክለቦችን ማልያ ለብሼ ተጫውቻለው፡፡ በነበረኝ ቆይታ ጥሩ የሚባል ጊዜ አሳልፌያለው ፤ የዛኑም ያህል ጥሩ የማይባል ጊዜ አሳልፌለው፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ትምህርት አግኝቼባቸዋለው፡፡ አሁን ላለሁበት የእግር ኳስ ህይወቴም ጥሩ የሆነ ልምድ አግኝቼባቸዋለው፡፡


በባህሪህ አስቸጋሪ ነህ ትባላለህ…?

ያን ያህል መጥፎ የሚባልና አስቸጋሪ ባህሪ እንደሌለኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሰው እንዴት እንደሚረዳኝ አላውቅም፡፡ በእግር ኳስ የሚያጋጥሙ ነገሮች ለምሳሌ ከጨዋታ ታክቲክ ጋር ነፃነት ተሰቶኝ ካልተጫወትኩ አዳንዴ አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል እንጂ ከአሰልጣኞች ፣ ከተጨዋቾች እና ከደጋፊዎች ጋር መልካም የሚባል ግኑኝነት ነው ያለኝ፡፡


የአርባምንጭ ቆይታህን እንዴት ታየዋለህ?

ከአርባምንጭ ጋር ያለኝ ቆይታ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የአርባምንጭን ማልያ ለብሼ የመጫወት እድል አላገኘሁም ይህ የመጀመርያዬ ነው። ነገር ግን ከቡድኑ ጋር ለመላመድ ብዙ አልተቸገርኩም፡፡ ምክንያትም አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች በፕሮጀክት አብረን ስንሰራ የማውቃቸው በመሆናቸው ቶሎ ተላምጄ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ እገኛለው፡፡


በአርባምንጭ በፍጥነት ልዩነት ፈጣሪ ተጨዋች ሆነሃል፡፡ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ከማቀበል በተጨማሪ ጎል በማስቆጠር መልካም ጊዜ እያሳለፍክ ትገኛለህ . . .

አዎ፡፡ በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ይህም የሆነው ስራዬን ጠንክሬ በመስራቴና የቡድን አጋሮቼ በሚያደርጉልኝ እገዛ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሰልጣኞቼ የሰጡኝ የጨዋታ ነፃነት ያለኝን አቅም እንዳሳይ ረድቶኛል፡፡ ሁሌም ከጎኔ በመሆን እያበረታቱኝ የሚገኙት የአርባምንጭ ደጋፊዎች እገዛም ትልቅ ነው፡፡ ሁሉንም በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለው፡፡

የጥሩ ክህሎት ባለቤት ነህ፡፡ ይህን እንዴት ማዳበር ቻልክ?

ከልጅነታችን ጀምሮ ምሳሌ የሆኑን የቀድሞ የአርባምንጭ ከተማ ተጨዋቾች አሉ፡፡ እነሱን እያየን ማደጋችን እና ሁልጊዜ ራሴን ከዘመናዊ እግር ኳስ ጋር እያላመድኩ ለመሄድ የማደርገው ጥረት የተሰጥኦዬ ሚስጢር ነው፡፡


ከአርባምንጭ ጋር ምን ታስባለህ?

የመጀመርያዎቹ ሳምንታት ላይ አጀማመራችን ጥሩ አልነበረም፡፡ አሁን በጥሩ መንገድ ላይ ነው ያለነው፡፡ ህብረታችን ደስ ይላል፡፡ በሁለተኛው ዙር በጉዳት ያጣናቸው ተጨዋቾች ሲመለሱ በሚገባ ተጠናክረን ጥሩ ውጤት እናስመዘግባለን ብዬ አስባለው፡፡


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *