የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት

የቅዱስ ጊዮርጊስ አስደናቂ ግስጋሴ በሪከርድ እየታጀበ ነው ፤ የወላይታ ድቻ እና ‹ አቻ › ወዳጅነት ቀጥሏል ፤ የኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት ጨዋታ ራሱን በሌላ መልክ ደገመ ፣ ደደቢት መጥፎ ሪኮርዶቹን እያሻሻለ ነው . . . ሶከር ኢትዮጵያ የ1ኛው ሳምንት ክንውኖችን በእውነታዎች አስደግፋ እንዲህ አሰናድታዋለች፡፡


– የዘንድሮው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁሉም ረገድ አስደናቂ ነው፡፡ ፈረሰኞቹ ባለፈው እሁድ ሙገርን ሲያሸንፉ በሊጉ ለተከታታይ 12ኛ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ፈረሰኞቹ በ2000 እና 2002 የውድድር ዘመኖች በተከታታይ 11 የሊግ ጨዋታዎችን ያሸነፉበትን ሪኮርድ በ1 አሻሽለው 2ኛ ምርጥ ሪኮርዳቸውን አሻሽለዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጣዮቹን 5 ጨዋታዎች በተከታታይ ማሸነፍ ከቻለ በ1991/92 የውድድር ዘመን የያዙትን በ15 ተከታታይ ጨዋታዎችበተከታታይ የማሸነፍ ሪኮርድ ይሰብራሉ

(ጨዋታዎቹ የተሰሉት በተጫወቱበት ቀን ሳይሆን በመደበኛ መርሃ ግብራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ በወላይታ ድቻ የተሸነፈው በመጋቢት ወር ቢሆንም መርሃ ግብሩ የ2ኛው ሳምንት ነው)

– ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታ ግብ ሳያስቆጥር ከወጣ 1 አመት አልፎታል፡፡ ፈረሰኞቹ ለመጨረሻ ጊዜ ግብ ሳያስቆጥሩ የወጡት ሚያዝያ 3 ቀን 2005 በኢትዮጵያ ቡና 1-0 በተረቱበት ጨዋታ ነው፡፡ ከዛ ወዲህ ባደረጓቸው 26 ተከታታይ ጨዋታዎች ቢያንስ 1 ግብ በየጨዋው አስቆጥረው ወጥተዋል፡፡

– ፈረሰኞቹ የእሁዱን 4 ግቦች ጨምሮ በተጋጣሚያቸው ላይ 29 ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ ይህ መጠን በደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻውን አራት ደረጃ ከያዙት ክለቦች የግብ ድምር በ1 ይበልጣል፡፡

– የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ ለብቻው ከ7 ክለቦች የበለጡ የሊግ ግቦች አስቆጥሯል፡፡

-መከላከያ ካለፉት 8 ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማግኘት ተስኖታል፡፡ ጦሩ ህዳር 29 ቀን 2006 ኢትዮጵያ መድንን በሳሙኤል ታዬ እና መድህኔ ታደሰ ግቦች 2-0 ካሸነፈ ወዲህ 4 ጨዋታ ተሸንፎ 4 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት አጠናቋል፡፡ የእሁዱ የሲዳማ ቡና ሽንፈት በ4 ጨዋታ 3ኛው ነው፡፡

– ወላይታ ድቻ በውድድር ዘመኑ 14 ጨዋታዎች ብቻ 10 አቻዎችን አስመዝግበዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሰባቱ ጨዋታዎች ካለምንም ግብ አቻ የወጡባቸው ነው፡፡

– የማይዘሙት ምሰሶዎች በመጠኑ እያንሰራሩ ነው፡፡ መብራት ኃይል ሀዋሳ ከነማ ላይ ስመዘገበውን ድል ተከትሎ የነጥብ ድምሩን 12 አድርሷል፡፡ መብራት ኃይል ከ12 ነጥቦች 7ቱን ያሳኩት ባለፉት 4 ጨዋታዎች ነው፡፡ በአስገራሚ ሁኔታ ቀሪዎቹ 5 ነጥቦች የተገኙት ባለፉት 10 ጨዋታዎች ነው፡፡

– ኢትዮጵያ ቡና ደደቢትን 4-1 በማሸነፍ የአምናውን ሽንፈት ተበቅሏል፡፡ ከድሉ በበለጠ የባለፈው አመት እና የዘንድሮው የውድድር ዘመን የተገላቢጦሽ ቢሆንም ያለው መመሳሰል አስገራሚ ነው፡፡ አምና በመጀመርያው ዙር ደደቢት 2-1 ሲያሸንፍ ዘንድሮ ኢትዮጵያ ቡና በመጀመርያው ዙር በተመሳሳይ 2-1 አሸንፏል፡፡ በሁለተኛው ዙርም አምና ደደቢት 4-1 ሲያሸንፍ የዘንድሮው ተራ ለኢትዮጵያ ቡና ሆኗል፡፡

– መብራት ኃይል ከ ሀዋሳ ከነማ ያደረጉት ጨዋታም አስገራሚ መመሳሰል ነበረው፡፡ በመጀመርያው ዙር ጨዋታ መብራት ኃይል 2-1 ሲያሸንፍ በሁለተኛውም በተመሳሳይ ወውጤት አሸንፏል፡፡ በሁለቱም ዙሮች ቀድመው ግብ ያስቆጠሩት ሀዋሳ ከነማዎች ሲሆኑ በሁለቱም ጨዋዎች የአሸናፊነቱን ግብ ያስቆጠረው ተሸመ ኦሼ ነው፡፡

– አምና በ2ኛው ባልተገባ ስፖርታዊ ባህርይ የኢትዮጵያ ቡናው ፋሲካ አስፋው በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲባረር ዘንድሮ በተመሳሳ የደደቢቱ ብርሃኑ ቦጋለ በአላስፈላጊ ባህርይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡

– ደደቢት በውድድር ዘመኑ የመጀመርያ 14 ሳምታት ይህንን ያህል ከፍተኛ የሽንፈት መጠን አስመዝግቦ አያውቅም፡፡ ደደቢት ዘንድሮ እስካሁን 5 ጨዋታዎች በሽንፈቴ ሲያጠናቅቅ አምና ሻምፒዮን ሲሆን በሙሉ የውድድር ዘመኑ ካስመዘገበው በ2 የበለጠ ሽንፈት ከወዲሁ አስተናግዷል፡፡

– ኢትዮጵያ ቡና እንዲህ አይነት ወጥ አቋም ያሳየባቸው አጋጣሚዎች ብዙ አይደሉም፡፡ የትላንቱን ድል ጨምሮ በተከታታይ 5ኛ ድሉን አስመዝግቧል፡፡ ቀሪ ጨዋታዎችን ጨምሮ 8 ተከታታይ ጨዋታዎችን ድል ነስቷል፡፡ የትላንቱ ድል ለአደገኞቹ በመደበኛ መርሃ ግብር ያስመዘገቡት 5ኛ ተከታታይ ድላቸው ነው፡፡ ቀጣዮቹን 2 ጨዋታዎች ካሸነፉ በ1999 የተያዘውን የክለቡን ሪኮርድ ያሻሽላሉ፡፡

– ደደቢት ከ3 ግቦች በላይ አስተናግዶ ሲሸነፍ በ2002 ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡

– ዘንድሮ ሲዳማ ቡና በሜዳው ሽንፈት አላስተናገደም፡፡ 7 ክለቦችን ወደ ይርጋለም ጋብዞ 5 ጨዋታዎችን አሸንፏል፡፡ በቀሪዎቹ አቻ ተለያይቷል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የተሸነፈውም አምና በውድድር አመቱ የመጨረሻ ጨዋታ በመብራት ኃይል 1-0 ነው፡፡

{jcomments on}

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *