በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ትላንት በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች አርባምንጭ እና ሐረር ድል ቀንቷቸዋል፡፡ በአዲስ አበባ ስታዲየም 9፡00 በተጀመረው የመከላከያ እና የአርባምንጭ ከነማ ጨዋታ አርባምጭ ከነማ በግበረ ሚካኤል ያእቆብ የ83ኛ ደቂቃ ግብ 1-0 አሸንፎ ወጥቷል፡፡ ገብረሚካኤል በውድድር ዘመኑ ግብ ሲያስቆጥር የመጀመርያው ግብ ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡በጨዋታው ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን አልፎ አልፎ ሁለቱም ቡድኖች የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር፡፡
መከላከያ በውጤት ቀውስ ውስጥ መዳከሩን ቀጥሏል፡፡ በጨዋታው ከዚህ ቀደም የሚያሳዩትን የጨዋታ ፍሰት እና የማሸነፍ ፍላጎት አጥተው የዋሉ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ሲሳይ ደምሴ በቀይ ካርድ ከሜዳ መወገዱም በውጤታቸው ላይ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
ቀጥሎ በተካሄደው እና ፈጣን እንቅስቃሴዎች በተካሄዱበት የመድን እና ሐረር ሲቲ ጨዋታ የምስራቁ ክለብ አሸንፎ ላለመውረድ የሚያደርገውን ፉክክር አጠናክሯል፡፡ ለሐረር ሲቲ የድል ግቦቹን ገዛኸኝ እንዳለ እና ሚካኤል ወልደሩፋኤል ሲያስቆጥሩ ዳዊት ሞገስ ለመድን አስቆጥረዋል፡፡ ገዛኸኝ እንዳለ በ27ኛው ሴኮንድ ከመረብ ያሳረፋት የሐረር ሲቲ ቀዳሚ ግብ የዘንድሮ ፈጣን ግብ ሆና ተመዝግባለች፡፡
ሐረር ሲቲ በሁለተኛው ዙር በግል ባለሃብቶች ከተዛወረ ወዲህ በጥሩ መነቃቃት ላይ ይገኛል፡፡ ቡድኑ ሲያሸንፍ ለተጫዋቾች ይሰጠው የነበረው ማበረታቻ ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩና አስተዳደራዊ ቀውሱ በመቀረፉ ቡድኑ በአዲስ መንፈስ እና በሙሉ የራስ መተማመን ጨዋታዎችን ማከናወን ጀምሯል፡፡ በሁለት ጨዋታዎች የታየው ውጤትም ይህን የሚያሳይ ነው፡፡
ከድሎቹ በኋላ አርባምንጭ ከነማ ደረጃውን ወደ 6 ከፍ ሲያደርግ ሐረር ሲቲ ካለፉት 2 ጨዋታዎች ያገኘውን 4 ነጥብ ተጠቅሞ የነጥብ ድምሩን 13 አድርሷል፡፡
ሊጉ ዛሬና ነገም ሲቀጥል በ9 ሰአት ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናግዳል፡፡ ሀዋሳ ላይ ደግሞ ሀዋሳ ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን በተመሳሳይ ሰአት ያስተናግዳል፡፡ እሁድ ደደቢት አዲስ አባባ ላይ ሲዳማ ቡናን 11፡00 ላይ ሲያስተናግድ ፋሲለደስ ላይ በ10 ሰአት ዳሽን ቢራ ከ ሙገር ሲሚንቶ ይጫወታሉ፡፡
{jcomments on}