የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የወልድያ የሁለተኛው ዙር መክፈቻ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል ። የአቻ ውጤቱን ተከትሎም የቡድኑ አሰልጣኞች ስለጨዋታው ያላቸውን አስተያየት ለጋዜጠኞች እንደሚከተለው ገልፀዋል ።
አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
” በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ መንቀሳቀስ ችለን ነበር ። ወደጎል ባንቀይራቸውም ብዙ የግብ ዕድሎችንም ፈጥረን ነበር ። በሁለተኛውም አጋማሽም እንዲሁ በመልሶ ማጥቃት እድሎችን ለመፍጠር ሞክረን ነበር ። ሆኖም ግን መጠቀም አልቻልንም ። ቢሆንም ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ተሸንፈን እንደመምጣታችን ውጤቱ በጣም ጥሩ ባይባልም ከሽንፈቱ ስነልቦና ከመውጣት አንፃር ጥሩ የሚባል ነው ። በቀጣይ ያስፈረምናቸው እና ለዚህ ጨዋታ ያልደረሱልንን ተጨዋቾች ከቀጣዩ ሳምንት ጀምረን በመጠቀም ቡድኑን ወደ መልካም ውጤት ለማምጣት ይምንሰራ ይሆናል ።”
አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ – ወልድያ
” የዛሬው ጨዋታ ተመጣጣኝ ነበር ። ወደ ጎል በመድረስ ግን እኛ የተሻልን ነበርን ። እንቅስቃሴያችንም ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ነበር ። ጎል የማግባት አቅማችን አሁንም ትንሽ ወረድ ያለ ነው ። በዚህ በኩል ብዙ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች አሉ ። ያገኘናቸውን ኳሶች አለመጠቀማችንም ዋጋ እያስከፈለን ነው ። አንድ ሁለት የሚሆኑ አዲስ ተጨዋቾችን ለማስገባት ሞክረናል ሆኖም የነበረን ጊዜ አጭር በመሆኑ ችግሮቻችንን ሙሉ ለሙሉ አልቀረፍንም ። ቡድኑ የመጀመሪያ ዕቅዱ በሊጉ መቆየት እንደመሆኑ መጠን በመከላከሉ ከሚያሳየው ጥንካሬ በተጨማሪ በተጋጣሚዎች ላይ ብልጫ ለመውሰድ እና ጎሎችን ለማስቆጠር ጠንክረን መስራት ይኖርብናል ። “