ፕሪምየር ሊጉ ዛሬ በ6 ጨዋታዎች ይቀጥላል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትላንት በተደረጉ ሁለት ግብ አልባ ጨዋታዎች የሁለተኛውን  ዙር ጀምሯል፡፡ ዛሬም በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች 6 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ደደቢት ከ ኢትዮጵያ ቡና በ09:00 የሚያደርጉት ጨዋታ በ16ኛው ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ ነው፡፡

ደደቢት በውድድር ዘመኑ ሁለት ሽንፈት ብቻ በማስመዝገብ 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ጨዋታውን ማሸነፍ በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ፍጥነቱን እንዲጨምር እና በቀጣዩ ሳምንት ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ መነሳሻ ይሆነዋል፡፡ በምርጥ አቋም ላይ ለሚገኘው ኢትዮጵያ ቡናም ይህን ጨዋታ በድል ማጠናቀቅ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ይበልጥ ለመጠጋት የሚረዳው በመሆኑ ከፍተኛ ፉክክር ከጨዋታው ይጠበቃል፡፡

ይህንን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው እንዲመራ ተመድቧል፡፡

አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ አዲስ አበባ ከተማ የአንደኛውን ዙር የበላይነት ለመድገም በማለም ሀዋሳ ከተማን ያስተናግዳል፡፡ ሁለቱ ክለቦች የመጀመርያውን ዙርም በተመሳሳይ የሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ (ሀዋሳ) የተጫወቱ ሲሆን ሁለቱም በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለመውሰድ የሚጥሩ እንደመሆናቸውና በወራጅነት ስጋት ውስጥ እንደመገኘታቸው ሊታይ የሚገባው ጨዋታ ነው፡፡ ይህን ጨዋታ ፌዴራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል፡፡

አርባምንጭ ከተማ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በሳምንቱ ከሚጠበቁት ጨዋታዎች አንዱ ነው፡፡ ጨዋታው ዘንድሮ ከክልል ጨዋታዎች ድል ባላስመዘገበው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ሽንፈት ባላጋጠመው አርባምንጭ ከተማ መካከል የሚካሄድ ይሆናል፡፡ ከአርባምንጭ ወንድወሰን ሚልኪያስ ፣ ከቅዱሰ ስጊዮርጊስ አብዱልከሪም ንኪማ ፣ ደጉ ደበበ ፣ ምንያህል ተሾመ እና ሳላዲን ሰኢድ የማይሰለፉ ሲሆን ጨዋታውንም ኢንተርናሽናል አርቢቴር ለሚ ንጉሴ ይመራዋል፡፡

ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ፋሲል ከተማ በቅርብ ርቀት የሚከተለው ሲዳማ ቡናን ያስተናግዳል፡፡ በሁለቱ ክለቦች መካከል ያለው የነጥብ ርቀት 1 ብቻ በመሆኑ ከፍተኛ የመሸናነፍ ፉክክር ይጠበቃል፡፡ አብዱራህማን ሙባረክ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆን ዮሃንስ ሽኩር ከ5 ሳምንታት ጉዳት በኋላ በፋሲል የጎል ብረቶች መሀል እንደሚቆም ይጠበቃል፡፡ በሲዳማ ቡና በኩል ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል፡፡

ይህን ጨዋታ ከአፍሪካ ዋንጫው በኋላ የመጀመርያ የሊግ ጨዋታውን በሚዳኘው ኢንተርናሽናል አርቢቴር ባምላክ ተሰማ ይመራል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ ድሬዳዋ ስታድየም ላይ አዳማ ከተማን ያስተናግዳል፡፡ በዋንጫ ፉክክሩ እና ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ለአዳማ ከተማው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የመጨረሻው ይሆናል፡፡ አዳማ አሁንም የአምበሉን ሱሌይማን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን በድሬዳዋ በኩል የጉዳት ዜና የለም፡፡ ያዘዋወራቸው አዳዲስ ተጫዋቾችን ይጠቀማል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ፌዴራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ይመራዋል፡፡

በ16ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የሚሆነው በ11:30 መከላከያ ከ ወላይታ ድቻ የሚያደርጉት ጨዋታ ነው፡፡ ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ከድል የራቁት ሁለቱ ክለቦች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይህ ጨዋታ አስፈላጊ ነው፡፡ ቢንያም ወርቅአገኘሁ ጨዋታውን የሚመራው ዳኛ ነው፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ ሁሉንም ጨዋታዎች ቦጥታ የውጤት መግለጫ ወደ እናንተ የምታደርስ ሲሆን ደደቢት ከ ኢትዮጵዳ ቡና እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉትን ጨዋታ በቀጥታ የፅሁፍ ስርጭት ታደርሳችኋለች፡፡

[table id=198 /]

[league_table 10415]

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *