ደካማ አንደኛ ዙር ያሳለፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሁለተኛው ዙር ተሻሽሎ ለመቅረብ በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡ ደረጄ መንግስቱ ፣ ሮቤል ግርማ እና ጥላሁን ወልዴንም ማስፈረም ችሏል፡፡
በ2008 ባንክን ለቆ ወደ ዳሽን ቢራ ያመራው ደረጄ መንግስቱ አምና በዲሲፕሊን ግድፈት የአንድ አመት ቅጣት ተላልፎበት ከጨዋታ ርቆ ቆይቷል፡፡ አማካዩ ቅጣቱን በመጨረሱ እና ክለብ አልባ በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተመልሶ ትላንት ቡድኑ ከወልድያ ባደረገው ጨዋታ መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል፡፡
ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የተለያየው ሮቤል ግርማ ሌላው ክለቡን የተቀላቀለ ተጫዋች ነው፡፡ ፋሲል ከተማን ለቆ ድሬዳዋ ከተማን ዘንድሮ የተቀላቀለው ሮቤል ባንክን የተቀላቀለው በቋሚ ዝውውር ነው፡፡
ጥላሁን ወልዴ ንግድ ባንክን የተቀላቀለ ሌላው ተጫዋች ነው፡፡ አማካዩ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ኢትዮጵያ ቡናን ለቆ አዳማ ከተማን ቢቀላቀልም ከ6 ወራት በኋላ ከክለቡ ጋር ተለያይቶ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በቋሚ ኮንትራት መቀላቀል ችሏል፡፡
አምሀ በለጠ እና ዳኛቸው በቀለን የለቀቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ከሶስቱ አዲስ ፈራሚዎች በተጨማሪ አቢኮይ ሻኪሩን ያስፈረመ ሲሆን በርካታ ክፍተቶች ያሉበት ቡድን እንደመሆኑ ዝውውሮቹ ክፍተቶችን ለመድፈን አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል፡፡